ቀጥታ፡

ለህዝቦች ሰላምና ትስስር መጠናከር የንግዱ ዘርፍ ሚና የላቀ መሆኑ ተገለጸ

ሰመራ፤ የካቲት 14/2016 (ኢዜአ) ፡-ለህዝቦች ሰላምና ትስስር መጠናከር የንግዱ ዘርፍ ሚና የላቀ መሆኑን በሰላም ሚኒስቴር የሰላም ግንባታ ዴስክ ሃላፊ አቶ ወንዶሰን መኮንን አስታወቁ።

በአፋር፣ አማራና ትግራይ ክልሎች የንግድ እንቅስቃሴን ለማነቃቃትና አጠናክሮ ለማስቀጠል ዓላማ ያደረገ የፓናል ውይይት ዛሬ በሰመራ ከተማ እየተካሄደ ነው።

በሰላም ሚኒስቴር የሰላም ግንባታ ዴስክ ሃላፊ አቶ ወንዶሰን መኮንን በወቅቱ እንደገለጹት፤ በህዝቦች መካከል ሰላምና የእርስ በርስ ግንኙነትን ለመፍጠርና ለማጠናከር የንግዱ ዘርፍ ሚና ከፍተኛ ነው ።


 

ሚኒስቴሩ የንግዱ ዘርፍ ለሰላም ግንባታና ለህዝቦች ትስስር ያለውን ሚና እንዲወጣ ለማስቻል ከአጋር አካላት ጋር እየሰራ መሆኑንም አመልክተዋል ።

የአፋር ክልል የንግድና ዘርፍ ማህበራት  ምክር ቤት ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ዳውድ ሃመሎ በበኩላቸው፤ ቀደም ብሎ በነበረው ችግር በክልሎቹ መካከል የንግድ እንቅስቃሴና ግንኙነት ተቀዛቅዞ መቆየቱን ተናግረዋል።

ችግሩን ለማቃለል የዘርፉ ባለድርሻ አካላት ሚና ከፍተኛ መሆኑን ጠቁመው፤ በተለይም “በየደረጃው የምንገኝ ማህበራት በትብብር ሚናችንን ልንወጣ ይገባል” ብለዋል።

በክልሎቹ መካከል ያለው የንግድ ግንኙነት እንዲነቃቃና እንዲጠናከር በማድረግ ረገድ ውይይቱ ወሳኝ ሚና እንዳለው አመልክተዋል።

በፓናል ውይይቱ የሰላምና የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች ተወካዮች እንዲሁም የኢትዮጵያ ነጋዴ ሴቶች ማህበር ፕሬዝዳንት ተሳትፈዋል።

እንዲሁም  የሀገራዊ ምክክር ኮሚሸነር፣ የሶስቱ ክልሎች የንግድ ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት አባላትና ነጋዴ ሴቶች ፕሬዝዳንቶች እንዲሁም የአፋር ክልል ንግድና ኢንዲስትሪ፣ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ የስራ ሃላፊዎችን ጨምሮ ጥሪ የተደረገላቸው ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል ።

የፓናል ውይይቱ የጋራ የአቋም መግለጫ በማውጣት እንደሚጠናቀቅ በመርሀ ግብሩ ተመላክቷል።


 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም