በመዲናዋ ለአቅመ ደካሞች በሚደረገው ምገባ ባለሃብቶች ተሳትፏቸውን እንዲያሳድጉ ጥሪ ቀረበ - ኢዜአ አማርኛ
በመዲናዋ ለአቅመ ደካሞች በሚደረገው ምገባ ባለሃብቶች ተሳትፏቸውን እንዲያሳድጉ ጥሪ ቀረበ
አዲስ አበባ፤ የካቲት 14/2016(ኢዜአ)፦ ለአቅመ ደካሞች በሚደረገው ምገባ ባለሃብቶች ተሳትፏቸውን እንዲያሳድጉና የወገን አለኝታነታቸውን እንዲያሳዩ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምገባ ኤጀንሲ ጥሪ አቀረበ።
በአዲስ አበባ በ2013 ዓ.ም በአንድ የምገባ ማዕከል የተጀመረው ስራ በአሁኑ ወቅት 20 የምገባ ማዕከላት ደርሷል።
የኤጀንሲው ምክትል ዳይሬክተር ስንታየሁ ማሞ ለኢዜአ እንዳስታወቁት፣ በመዲናዋ ምንም አይነት ገቢ የሌላቸው አቅመ ደካማ ዜጎች ቢያንስ በቀን አንድ ጊዜ ለመመገብ ርብርብ እየተደረገ ነው።
የምገባ ማዕከላቱ ስራቸውን በአግባቡ እንዲወጡና ቢያንስ በቀን አንድ ጊዜ አቅመ ደካሞችን መመገብ እንዲችሉ የባለድርሻ አካላት ድጋፍና እገዛ ወሳኝ መሆኑንም ነው ምክትል ዳይሬክተሯ ያነሱት።
በተለይም የግል ባለሃብቱ ያለውን ተሳትፎ በማሳደግ ለወገን አለኝታነቱን ማሳየትና የኢትዮጵያውያንን የመረዳዳት እሴት እንዲያጎለብት ጠይቀዋል።
በመዲናዋ አገልግሎቱን እየሰጡ ካሉ ማዕከላት ውስጥ የተስፋ ብርሃን አሙዲን ምገባ ማዕከል ስራ አስኪያጅ ሰላሙ ማሞ፣ ማዕከሉ በቀን ለ2 ሺህ 700 ዜጎች አገልግሎት እየሰጠ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
ይሁንና ካለው ፍላጎት አኳያ አገልግሎቱን ከፍ ለማድረግ ባለሃብቱ ድጋፉን እንዲያጠናክር ጥሪ አቅርበዋል።
የተስፋ ብርሃን ምገባ ማዕከል ቁጥር 9 ስራ አስኪያጅ ገመቺስ ዋቅጅራ፥ በምገባ ማዕከሉ ከ500 በላይ ነዋሪዎች ተጠቃሚ መሆናቸውን አንስተዋል።
እንዲህ አይነት የምገባ ማዕከላት በየቦታው ተደራሽ እንዲሆኑ ተቋማትና ባለሃብቶች በቅንጅት ሊሰሩ ይገባል ብለዋል።
የምገባ ማዕከላት ተጠቃሚ የሆኑት ሶፊያ አህመድ፣ በቀለ ካይረዲንና ግርማ ካሳ በማዕከሉ የሚያገኙት የምገባ አገልግሎት የኑሮ ጫናቸውን እንዳቀለለላቸው አንስተዋል።