የአፍሪካ ሀገራት የዲጂታል መታወቂያ ሥርዓትን ሙሉ ለሙሉ ተግባራዊ ለማድረግ በትኩረት መሥራት አለባቸው

235

አዲስ አበባ፤ የካቲት 14/2016 (ኢዜአ)፦ የአፍሪካ ሀገራት የዲጂታል መታወቂያ ሥርዓትን ሙሉ ለሙሉ ተግባራዊ በማድረግ ዘላቂ ምጣኔ ኃብታዊ እድገት ለማስመዝገብ መሥራት እንዳለባቸው ተመላከተ።

12ኛው በስታትስቲክስ ላይ ያተኮረ ውይይት በበይነ-መረብ በመታገዝ መካሄዱን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን(ኢሲኤ) ለኢዜአ በላከው መግለጫ አመላክቷል።

በኢሲኤ የቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን ዋና ኃላፊ ማክታር ሴክ የዲጂታል መታወቂያ የምጣኔ ኃብት እድገት ላይ እሴት እንደሚጨምር ገልጸዋል።

በተለይም የምጣኔ ኃብት ፍሰትን ሕጋዊ በማድረግ፣ አካታች የአገልግሎት አሰጣጥ ሥርዓት ማበረታታትና የዲጂታል የመረጃ ልውውጥ እንዲጨምር በማድረግ የሚኖረውን ሚናም ዘርዝረዋል።

ሀገራት የዲጂታል መታወቂያን ተግባራዊ በማድረግ እ.አ.አ በ2030፤ ከ3 እስከ 13 በመቶ ዓመታዊ የሀገር አጠቃላይ ምርታቸው ላይ እንደሚጨምሩ በዘርፉ የተሰሩ ጥናቶች እንደሚያመላክቱ ተናግረዋል።

የምጣኔ ሃብት እሴትን በመጨመር ብቻ ሳይሆን የትምህርት፣ ጤና የሥራ ገበያና ሌሎች አገልግሎቶችን በማበረታታትና አካታችነታቸው እንዲጨምር በማድረግ ትልቅ ፋይዳ እንዳለው አንስተዋል።

ውጤታማ የዲጂታል መታወቂያ ሥርዓት ትግበራን እውን ለማድረግ እንደየሀገራዊ ነባራዊ ሁኔታው ችግሮችን ለይቶ መፍታትና በዘርፉ ቅንጅታዊ አሰራሮች መጠናከር እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።

በኢሲኤ የአፍሪካ ስታቲስቲክስ ማዕከል ዳይሬክተር ኦሊቨር ቺንጋንያ በበኩላቸው የዲጂታል መታወቂያ ሥርዓት ሁሉም ዜጎች በፍትኃዊነት በመንግሥት መስተናገዳቸውን የሚያረጋግጥ መሆኑን ተናግረዋል።

በአፍሪካ 542 ሚሊየን ዜጎች የመለያ ካርድ እንዳሌላቸው ያመላከቱት ደግሞ በኢሲኤ የሥነ-ሕዝብና ማኅበራዊ ስታትስቲክስ ዋና ኃላፊ ዊሊያም ሙህዋቫ ናቸው።

ከእነዚህ መካከል እድሚያቸው ከአምስት ዓመት በታች የሆኑ 95 ሚሊየን ሕጻናት የልደት ምዝገባ ያላደረጉ ሲሆን 120 ሚሊየን ደግሞ የልደት ካርድ የላቸውም ብለዋል።

ሀገራት ሁሉም ሰው ሕጋዊ የመሆን መብቱን ለማረጋገጥ የፖለቲካ ቁርጠኝነት፣ የተቋማት ግንባታና ግንዛቤ መፍጠር ላይ መሥራት እንዳለባቸውም ጠቁመዋል።

ኢትዮጵያ የዲጂታል መታወቂያ ሥርዓትን በመዘርጋት ነዋሪዎች የመታወቅ መብታቸው እንዲረጋገጥና ሌሎች መብቶችን የመጠቀም እድሎችን ለማስፋት የዲጂታል መታወቂያ አዋጅን ከ2015 ዓ.ም ጀምሮ ተግባራዊ እያደረገች ትገኛለች።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም