መረጃዎች በቀላሉ ተደራሽ ለማድረግ የሚያስችል ዘመናዊ የአሰራር ሥርዓት ለመዘርጋት እየተሰራ ነው - ኢዜአ አማርኛ
መረጃዎች በቀላሉ ተደራሽ ለማድረግ የሚያስችል ዘመናዊ የአሰራር ሥርዓት ለመዘርጋት እየተሰራ ነው
አዲስ አበባ፤ የካቲት 14/2016(ኢዜአ)፦ መረጃዎች በቀላሉ ተደራሽ ለማድረግ የሚያስችል ዘመናዊ የአሰራር ሥርዓት ለመዘርጋት እየተሰራ መሆኑን የኢትዮጵያ ቤተ-መዛግብትና ቤተ-መጻሕፍት አገልግሎት ገለጸ።
ተቋሙ የ80ኛ ዓመት የምስረታ በዓሉንና የመዛግብት ሕንጻ ምርቃትን አስመልክቶ ለመገናኛ ብዙኃን ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥቷል።
የተቋሙ ዋና ዳይሬክተር ይኩኖአምላክ መዝገቡ በዚሁ ጊዜ እንደገለጹት፤ አገልግሎቱ የእውቀት ኃብት የሆኑ ክምችቶች የሚሰበሰቡበት፣ የሚደራጁበትና ተደራሽ የሚሆኑበት ነው።
ተቋሙ በኢትዮጵያ በማኅበራዊ፣ በኢኮኖሚያዊና በፖለቲካዊ ሂደቶች ውስጥ ትልቅ አሻራ ያሳረፉ ግለሰቦች መፍለቂያ መሆኑን ጠቁመዋል።
የተቋሙ ተጠቃሚዎች ቁጥር ከጊዜ ወደጊዜ እያደገ መምጣቱን ጠቅሰው ተቋሙ አገልግሎቱን ለማሻሻል እየሰራ መሆኑን ነው የገለጹት።
ይህንንም ታሳቢ በማድረግ ባለ 17 ወለል ሕንጻ ያስገነባ ሲሆን የፊታችን ቅዳሜ እንደሚያስመርቅ ተናግረዋል።
ግንባታው 700 ሚሊየን ብር ወጪ እንደተደረገበት ያነሱት ዋና ዳይሬክተሩ ሙሉ በሙሉ በመንግሥት እንደተሸፈነም ተናግረዋል።
ዘመኑ የደረሰበትን የቤተ-መዛግብትና ቤተ-መጻህፍት ቴክኖሎጂዎችን ያካተተው ይኸው ሕንጻ የፊታችን ቅዳሜ የካቲት 16 ቀን 2016 ዓ.ም ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች በተገኙበት ይመረቃል ብለዋል።
ተቋሙ በአንድ ግቢ የተወሰነ አለመሆኑን ገልጸው በክልሎች እንዲሁም በማረሚያ ቤቶች ጭምር አገልግሎት እየሰጠ እንደሚገኝ ጠቁመዋል።
በቀጣይም አገልግሎቱ ያሉትን መረጃዎች በቀላሉ ለማግኘት የሚያስችሉ ሥርዓቶች ለመዘርጋትም ሙከራዎች እየተደረጉ መሆኑንም አንስተዋል።
የኢትዮጵያ ቤተ-መዛግብትና ቤተ-መጻሕፍት አገልግሎት በ1936 ዓ.ም ነበር ወመዘክር የሕዝብ ቤተ-መጻሕፍት ተብሎ የተቋቋመው።