ኢትዮጵያ ለፓን-አፍሪካኒዝም መጎልበት እና ለአፍሪካ ሀገራት ነጻነት የዋለችው ውለታ ለዲፕሎማሲዋ መጎልበት ወረት ሆኖ እያገለገለ ነው- የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ ለፓን-አፍሪካኒዝም መጎልበት እና ለአፍሪካ ሀገራት ነጻነት የዋለችው ውለታ ለዲፕሎማሲዋ መጎልበት ወረት ሆኖ እያገለገለ ነው- የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር
አዲስ አበባ፤ የካቲት 14/2016(ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ ለፓን-አፍሪካኒዝም መጎልበት እና ለአፍሪካ ሀገራት ነጻነት የዋለችው ውለታ ለዲፕሎማሲዋ መጎልበት ወረት ሆኖ እያገለገለ መምጣቱን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ገለጸ።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዶክተር መለስ ዓለም በሳምንታዊ መግለጫቸው እንዳሉት፣ ከአፍሪካ ሕብረት የመሪዎች ጉባኤ በተጓዳኝ ውጤታማ የሁለትዮሽ ዲፕሎማሲያዊ ስራዎች ተከናውነዋል።
ከአንጎላና ከደቡብ አፍሪካ ጋር የተፈረሙ ስምምነቶችን ከሳምንቱ ዲፕሎማሲያዊ ስኬቶች መካከል ለአብነት ጠቅሰው፥ የኢትዮጵያ ዲፕሎማሲ ወደ ከፍታ መውጣቱ በግልጽ የታየበት ሳምንት ነበር ብለዋል።
ኢትዮጵያ ብሪክስን መቀላቀሏ ከደቡብ አፍሪካ ጋር ያላትን ታሪካዊ ትብብር ይበልጥ ለማጠናከር የሚያስችል እና ለስምምነቱ ገቢራዊነት የመሪዎች ቁርጠኝነት የታዬበት እንደሆነ ተናግረዋል።
በተመሳሳይ በነዳጅ ሀብት ማውጣት ሰፊ ልምድ ካላት አንጎላ ጋር የተፈረመው ስምምነት ተሞክሮ ለመለዋወጥ ያስችላል ነው ያሉት።
ከኢትዮጵያ ጋር ታሪካዊ ወዳጅነት ካላት ዝምባብዌ ጋር ውጤታማ ምክክር መደረጉን ገልፀው፣ በግብርና፣ በማኑፋክቸሪንግ እና በሌሎችም መስኮች በጋራ ለመስራት መግባባት ላይ ስለመደረሱ ገልፀዋል።
በሌላ በኩል እንደቤተሰብ የሚተያይ ህዝብ ያላቸው ኢትዮጵያና ኬንያ የሚኒስትሮች የጋራ ኮሚሽን ስብሰባ መካሄዱን ጠቅሰው፥ ሀገራቱ በሰባት ዘርፎች ስምምነት መፈራረማቸውን ጠቅሰዋል።
ስምምነቱም በቱሪዝም፣ ባህልና ስፖርት፣ በዱር እንስሳት ጥበቃ፣ በአሳ ልማት፣ ፔትሮሊየም እና በማረሚያ ቤተ አገልግሎት እና በሲቪል ሰርቪስ አቅም ግንባታ በጋራ ለመስራት የሚያስችል ነው ብለዋል።
የቪዛ ጉዳይ ሌላው የስምምነቱ አካል መሆኑን ጠቅሰው፣ በ1958 ጀምሮ የተደረገው የቪዛ ነፃ ስምምነት በኤሌክትሮኒክስ አገልግሎት መልኩ እንዲከወን መከለሱን አንስተዋል።
ይህም ለዘመናት የነበረውን ወዳጅነት ይበልጥ ወደላቀ ደረጃ እንደሚያሸጋግር በመጠቆም።
የሁለቱ ሀገራት ወዳጅነት በፉክክር ሳይሆን በጋራ ተጠቃሚነት ላይ የተመሰረተ እና በመንግስታት ለውጥ የማይዋዥቅ ግንኙነት መሆኑን ቃል አቀባዩ ተናግረዋል።
በቀጣይ ሳምንት በኬንያ-ናይሮቢ በሚካሄደው ዓለም አቀፍ የአካባቢ ጥበቃ ስብሰባ ኢትዮጵያ ጠንካራ ተሳትፎ እንደምታደርግ አረጋግጠዋል።
ከሌሎችም የአፍሪካ ሀገሮች ጋር በተደረጉ ውይይቶችም የኢትዮጵያ የዲፕሎማሲ ማዕከልነት እንዲፀና ሀገራቱ ፍላጎት ማሳየታቸውንና ኤምባሲያቸውን ለማጠናከር መወሰናቸውን ገልፀዋል።
በተለይም ኢትዮጵያ ለፓን አፍሪካኒዝም መጎልበት እና ለአፍሪካ ሀገራት ነጻነት በተለያዩ ጊዜያት የዋለችው ውለታ ለዲፕሎማሲዋ መጎልበት ወረት ሆኖ እያገለገለ መሆኑን አንስተዋል።