በቢሾፍቱ ከተማ የዲጂታል አድራሻ ሥርዓት ተግባራዊ ሆነ 

285

አዲስ አበባ፤ የካቲት 14/2016(ኢዜአ)፦ በኢትዮጵያ የስፔስ ሳይንስና ጂኦ-ስፓሻል ኢንስቲትዩት የለማው የዲጂታል አድራሻ ሥርዓት በቢሾፍቱ ዛሬ ተመርቆ ወደ ሥራ ገባ።   

በማስጀመሪያው መርኃ-ግብር የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዶክተር በለጠ ሞላ ጨምሮ የስፔስ ሳይንስና ጂኦስፓሻል ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር አብዲሳ ይልማ፣ የቢሾፍቱ ከተማ ከንቲባ አቶ አለማየሁ አሰፋ ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።

ዛሬ ተመርቆ የተጀመረው የዲጂታል አድራሻ ሥርዓት በከተማዋ የሚገኙ የተቋማትና መኖሪያ ቤቶችን ትክክለኛ መገኛ ሥፍራ ለማመላከት እንደሚረዳም ተጠቁሟል።

የመሬት አስተዳደርና ሌሎች የከተማዋን መረጃዎችን ለማዘመን እንደሚያስችልና አገልግሎት ሰጭ ተቋማትና የተገልጋዮችን መስተጋብር ምቹ የሚያደርግ እንደሆነም ተመላክቷል።

ዲጂታል የአድራሻ ሥርዓት ማንኛውንም አስተዳደራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ አገልግሎቶችን ቀልጣፋ በሆነ መንገድ ለሁሉም ተደራሽ ለማድረግ የሚያስችል ነው ተብሏል።

ቴክኖሎጂው ለነዋሪዎች ምቹ የሆኑ ከተሞችን ለመገንባት፣ ለጀማሪ የቴክኖሎጂ ሥራ ፈጣሪዎች ልዩ ልዩ የሥራ ዕድሎችን የሚፈጥርና የቱሪዝም ኢንዱስትሪውን የሚያሳድግ ነው ተብሏል።

በተጨማሪም የነዋሪዎችን ከቦታ ቦታ የሚደረግ እንቅስቃሴ ለማቃለል፣ቀልጣፋ ለማድረግና የኤሌክትሮኒክስ ግብይትን እውን ለማድረግ ጉልህ አስተዋጽዖ እንደሚያበረክት ተጠቁሟል።    

የዲጂታል አድራሻ ሥርዓት የከተሞች የአገልግሎት አሰጣጥን ማቀላጠፍን ጨምሮ የማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ  እንቅስቃሴን ለማዘመን እንደሚረዳም ተገልጿል።

የዲጂታል ኢኮኖሚ ግንባታውን በሚፈለገው ጥራትና ፍጥነት ተግባራዊ ለማድረግም የሚያስችል መሆኑንም እንዲሁ።

በአጠቃላይ የዜጎችን ሁለንተናዊ ደኅንነት በመጠበቅ  ለአንድ አገር ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ እድገት ያለው አስተዋጽኦ የጎላ እንደሆነ ተገልጿል። 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም