መንግስት ለሀገራዊ ምክክር ስኬታማነት ያልተቆጠበ ድጋፉን አጠናክሮ ይቀጥላል - ኢዜአ አማርኛ
መንግስት ለሀገራዊ ምክክር ስኬታማነት ያልተቆጠበ ድጋፉን አጠናክሮ ይቀጥላል
አዲስ አበባ፤ የካቲት 14/2016(ኢዜአ)፦ መንግስት ለሀገራዊ ምክክር ሂደት ስኬታማነት የሚያደርገውን ያልተቆጠበ ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥል በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግሥት ዋና ተጠሪ ሚኒስትር አቶ ተስፋዬ ቤልጅጌ ተናገሩ።
ሀገራዊ ምክክርን በብቃትና በገለልተኝነት ለመምራትና ለማስተባበር የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በአዋጅ ቁጥር 1265/2014 ተቋቁሞ ወደ ስራ ገብቷል።
የመንግስት ዋና ተጠሪ ሚኒስትሩ አቶ ተስፋዬ ቤልጅጌ ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ፤ ኢትዮጵያ ባለፈችባቸው የመንግስት አስተዳደር ሥርዓቶች በአንድ በኩል በመልካም የሚጠቀሱ በሌላ በኩል መደገም የሌለባቸው ግድፈቶች እንዳሉ አንስተዋል።
በዚህም ቀጣይነት ላለው የሀገረ መንግስት ግንባታ አስተማሪ ሁነቶችን የጋራ ለማድረግ፤ ግድፈቶችንም በሠላም፣ ዕርቅና ይቅርታ ለመዝጋት ቁጭ ብሎ መነጋገር ያስፈልጋል ብለዋል።
አሁን ያለው ትውልድም ነገን የተሻለ ለማድረግ የራሱን ታሪክ በመፃፍ ብሔራዊ መግባባት ለሰፈነባት ኢትዮጵያ አሻራውን ማሳረፍ እንደሚኖርበት ተናግረዋል።
በመንግስት ደረጃም የተለየ አቋም ያላቸው ሁሉ የጋራ አቋም የሚይዙበት መድረክ ለመፍጠር ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን አቋቁሞ ወደስራ እንዲገባ ማድረጉን አንስተዋል።
የኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን በርካታ ሂደቶችን አልፎ በአሁኑ ወቅት ለምክክሩ ወሳኝ የሆኑ ተግባራትነ እያከናወነ መሆኑን በሪፖርት እንዳሳወቀ ገልጸዋል።
ለዚህም በተለያዩ አካባቢዎች የአጀንዳና ተሳታፊ ልየታ ተግባርን በፍጥነት በማጠናቀቅ በተያዘው ዓመት ወደ ዋናው የድርድርና የውይይት መድረክ ለመግባት ዕቅድ መያዙንም ነው ያነሱት።
መንግስት ለሀገራዊ ምክክር ሂደቱ ስኬታማነት የሚያደርገውን ያልተቆጠበ ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥል ያረጋገጡት አቶ ተስፋዬ፥ ኢትዮጵያውያንም ለምክክሩ ውጤታማነት ሚናቸውን እንዲወጡ ጠይቀዋል።
በሀገራዊ ምክክሩ መሳካት የምታተርፈው ኢትዮጵያ ናት ያሉት አቶ ተስፋዬ፤ ኢትዮጵያውያን ጠንካራና ቅቡልነት ያለው ሀገረ መንግስት ለመገንባት ካላቸው ጽኑ ፍላጎት የተነሳ ምክክርን ይደግፉታል ብለዋል።
በአንጻሩ የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን የታለመለትን ግብ እንዳይመታ የሚያጥላሉ አንዳንድ አካላት መኖራቸውን ጠቅሰው፥ ድርጊታቸው ፋይዳ ቢስ እንደሆነ ገልጸዋል።
የምክክር ሂደቱ በቅድመ ዝግጅት፣ በዝግጅት፣ በምክክር ሂደት በትግበራና ክትትል ምዕራፍ የተከፋፈለ ሂደት እንዳለው በማንሳት፥ የኮሚሽኑ የስራ ኃላፊዎች ስራቸውን በገለልተኝነት እየተወጡ እንደሚገኙ ተናግረዋል።
በአሁኑ ወቅትም ኢትዮጵያውያን በጋራ ጉዳዮቻቸው ላይ ቁጭ ብለው ወደሚመክሩበት ምዕራፍ እየተሸጋገሩ ነው ብለዋል።