የኢትዮጵያ ቤተመዛግብትና ቤተመጻሕፍት አገልግሎት ያስገነባውን የመዛግብት ህንፃ የፊታችን ቅዳሜ ያስመርቃል - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ቤተመዛግብትና ቤተመጻሕፍት አገልግሎት ያስገነባውን የመዛግብት ህንፃ የፊታችን ቅዳሜ ያስመርቃል
አዲስ አበባ፤ የካቲት 14/2016(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ቤተመዛግብትና ቤተመጻሕፍት አገልግሎት ያስገነባውን ባለ 17 ወለል የመዛግብት ህንፃ የፊታችን ቅዳሜ እንደሚመረቅ አስታወቀ፡፡
የኢትዮጵያ ቤተመዛግብትና ቤተመጻሕፍት አገልግሎት የ80ኛ ዓመት የምስረታ በዓል እና የመዛግብት ህንጻ ምርቃትን አስመልክቶ ለመገናኛ ብዙኃን ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥቷል።
የአገልግሎቱ ዋና ዳይሬክተር አቶ ይኩኖአምላክ መዝገቡ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፥ አገልግሎቱ የእውቀት ሀብት የሆኑ ክምችቶች የሚሰበስቡበት፣ የሚደራጁበት እና ተደራሽ የሚሆኑበት ነው።
አገልግሎቱ በኢትዮጵያ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ ሂደቶች ውስጥ ትልቅ አሻራ ያሳረፉ ግለሰቦች መፍለቂያ መሆኑን ተናግረዋል።
ተቋሙ በየጊዜው አገልግሎቱን ለማሻሻል እየሰራ መሆኑን ገልጸው፥ የተጠቃሚዎች ቁጥር ከጊዜ ወደጊዜ እያደገ መምጣቱን ጠቅሰዋል።
ይህንንም ታሳቢ በማድረግ ባለ 17 ወለል ህንጻ ገንብቶ የፊታችን ቅዳሜ እንደሚያስመርቅ ተናግረዋል።
ግንባታው 700 ሚሊዮን ብር ወጪ እንደተደረገበት ያነሱት ዋና ዳይሬክተሩ፥ ሙሉ በሙሉ በመንግስት እንደተሸፈነም ተናግረዋል።
ዘመኑ የደረሰበትን የቤተመዛግብት እና ቤተመጻህፍት ቴክኖሎጂዎችን ያሟላው ይህ ህንጻ፥ የፊታችን ቅዳሜ የካቲት 16 ቀን 2016 ዓ.ም ከፍተኛ የመንግስት የስራ ኃላፊዎች በተገኙበት ይመረቃል ብለዋል።
የኢትዮጵያ ቤተመዛግብትና ቤተመጻሕፍት አገልግሎት በ1936 ዓ.ም ነበር ወመዘክር የህዝብ ቤተመጻሕፍት ሆኖ የተቋቋመው።