ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ የባህር በር የማግኘት ጥያቄ  ከዓለም አቀፍ ስምምነቶች ጋር የሚጣጣምና የሰጥቶ መቀበል መርህን የተከተለ ነው

አዲስ አበባ፤ የካቲት 14/2016(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ የባህር በር የማግኘት ጥያቄ  ከዓለም አቀፍ ስምምነቶች ጋር የሚጣጣምና የሰጥቶ መቀበል መርህን የተከተለ መሆኑን በውጭ ጉዳይ ኢንስቲትዩት ተመራማሪ የሆኑት አቶ አዲስ አለማው ገለጹ።

አገሮች የባህር ክልልና ወሰንን በምን መንገድ መጠቀም እንደሚገባቸው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት እ.ኤ.አ. በ1982 ዓለምአቀፍ የባህር ሕግ (United Nations Convention on the Law of the Sea/UNCLOS) አውጥቷል።

ይህን ሕግ ከ169 በላይ የአለምአገራት ተቀብለው ማጽደቃቸውንም ነው መረጃዎች የሚያመለክቱት።

ሕጉ እ.ኤ.አ. በ1994 ወደ ሥራ የገባ ሲሆን የጠረፍንና የዓለም አቀፍ ውኃ ክልል ምንነትና አጠቃቀም፣ እንዲሁም በባህር ወሰኖች የሚነሱ ውዝግቦችና የችግር አፈታት ሒደቶችን በዝርዝር የያዘ ነው።

በዚህ ሕግ በአገሮች የባህር ክልል ላይ የትኛውም አገር ለሰላማዊ ጉዳይ እስከሆነ ድረስ መተላለፊያ ሊከለክል እንደማይችል ተመላክቷል።

በዚህ ሕግ በተለይም አንቀጽ 125 ከተራ ቁጥር 1-5 ባለው ክፍል የባህር በር የሌላቸው አገሮች የባህር በር ባላቸው አገሮች በኩል በማንኛውም ዓይነት የመጓጓዣ መንገድ ከባህር ጋር የሚገናኙበት ነፃነት እንዳላቸው ይገልጻል።

በዓለም ላይ 44 አገራት የባህር በር አልባ መሆናቸውንና ከእነዚህም ውስጥ 16ቱ አገራት በአፍሪካ እንደሚገኙ መረጃዎች ያመለክታሉ።

በውጭ ጉዳይ ኢንስቲትዩት ተመራማሪ የሆኑት አቶ አዲስ አለማው ለኢዜአ እንዳሉት፥ ሕጉን መሰረት በማድረግ በርካታ የባሀር በር የሌላቸው ሀገራት የባህር በር ተጠቃሚ መሆናቸውን አስረድተዋል።

የባህር በር ባለቤት ከሆነው ሀገር ጋር በድርድር በመስማማት ለኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴዎችና ሌሎች ተግባራት መተላለፊያ በር ያገኙ ሀገራት እንዳሉም ነው የጠቀሱት።

የኢትዮጵያ የባህር በር የመጠቀም ጥያቄ ተገቢ መሆኑን ያነሱት ተመራማሪው፥ በተለይም እያደገ የመጣውን የህዝብ ቁጥርና ኢኮኖሚ መሸከም የሚችል የመግቢያና መውጫ በር ያስፈልጋታል ይላሉ።

ለዚህ መፍትሔ ለማምጣትም ዓለም አቀፍ የባህር በር የሚገኝባቸው ስምምነቶችን መሰረት በማድረግ በሰጥቶ መቀበል መርህ ወደብ የመጠቀም ጥያቄን እንዳቀረበችም አንስተዋል።

ኢትዮጵያ ከጎረቤት አገራት ጋር በትብብር ለመልማትና ለማደግ ፅኑ አቋም ያላትና ሰርታ የምታሳይ ሀገር መሆኗንም ጠቅሰው፥ ይህን ይበልጥ ውጤታማ ለማድረግም ሀገራቱ አማራጭ ወደብ የማግኘት ጥያቄዋን ሊቀበሉ እንደሚገባ ጠቁመዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም