በአማራ ክልል ሰላምን ዘላቂ ለማድረግ የተጀመሩ ስራዎች ተጠናክረው ይቀጥላሉ - ርዕሰ መስተዳድር አረጋ ከበደ - ኢዜአ አማርኛ
በአማራ ክልል ሰላምን ዘላቂ ለማድረግ የተጀመሩ ስራዎች ተጠናክረው ይቀጥላሉ - ርዕሰ መስተዳድር አረጋ ከበደ
ባህር ዳር፤ የካቲት 13/2016 (ኢዜአ)፡- በአማራ ክልል የተገኘውን ሰላም ዘላቂ ለማድረግ የተጀመሩ ስራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ አረጋ ከበደ አስታወቁ።
ርዕሰ መስተዳድሩ ዛሬ በተጀመረው የክልሉ ምክር ቤት ጉባኤ ላይ የክልሉን የአስፈፃሚ አካላት የስድስት ወራት ዕቅድ አፈፃፀም ሪፓርት አቅርበዋል ።
ርዕሰ መስተዳድሩ በወቅቱ እንደገለጹት፤ በክልሉ የፀጥታ ሁኔታውን ለማረጋጋት በታወጀው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መሰረት በተከናወነ ህግ የማስከበር ስራ በክልሉ መንግስትና ህዝብ ላይ የተጋረጠውን አደጋ መቀልበስ ተችሏል።
ርዕስ መስተዳድሩ አክለው አሁንም የክልሉ መንግስት ከሰላም ወዳዱ ህዝብና ከፀጥታ ሃይሉ ጋር በመሆን ክልሉን ወደ ተሟላ ሰላምና መረጋጋት የሚያደርስ ተግባራት እያከናወነ ይገኛል ብለዋል።
የሰላሙ ሁኔታ እየተሻሻለ መምጣቱን ተከትሎም ከክልል እስከ ወረዳ ለሚገኙ አመራር አባላት፣ ለፖሊስና ሚሊሺያዎች ስልጠና በመስጠት መልሶ የማደራጀት ስራ ተሰርቷል።
በቀድሞ የአማራ ልዩ ኃይል ውስጥ የነበሩ 6 ሺህ 491 አባላት ስልጠና ወስደው ወደ መደበኛ የመንግስት የፀጥታ መዋቅር እንዲገቡ ተደርጓል ሲሉም ለአብነት ጠቅሰዋል ።
ከዚሁ ጎን ለጎን የመንግስትን የሰላም ጥሪ ተቀብለው በመመለስ የተሃድሶ ስልጠና የወሰዱም ወደ ህዝቡ እንዲቀላቀሉ መደረጉን አመልክተዋል።
በክልሉ የተገኘውን ሰላም ዘላቂነት ለማረጋገጥም ህግ የማስከበር ስራው በተቀናጀ አግባብ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ርዕሰ መስተዳድሩ አስታውቀዋል።
ሰላምን ከማፅናት ጎን ለጎን በበጀት ዓመቱ የታቀዱ የልማትና የመልካም አስተዳደር ግቦችን ለማሳካት በህዝቡ፣ በአመራሩ፣ በፈፃሚውና በአጋር አካላት የተቀናጀ ውጤታማ ስራዎች እየተከናወኑ ናቸው ብለዋል።
በክልሉ የመጣውን ሰላም ተከትሎም ድርቅ በተከሰተባቸው አካባቢዎች በባለሙያዎች በተደረገ ጥናት ከ1 ነጥብ 8 ሚሊዮን በላይ ዜጎች የዕለት ምግብ እንደሚያስፈልጋቸው መለየቱን አስታውሰዋል።
በክልሉ መንግስት በኩልም እየተደረገ ያለውን ድጋፍ አብራርተዋል።
ለድርቅ ተጎጅዎች በፌዴራል መንግስት፣ በተለያዩ ረጂ ድርጅቶችና በሌሎች አካላት የምግብ ድጋፍ ተደራሽ ለማድረግ ጥረት እየተደረገ መሆኑን ርዕሰ መስተዳድሩ አስረድተዋል።
የምክር ቤት አባላትም በከሰዓት ውሎው በርዕሰ መስተዳድሩ በቀረበው ሪፖርት ላይ ጥያቄና አስተያየት በማቅረብ ውይይት አካሂደዋል።