ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ እና ኬንያ ትብብራቸውን  ይበልጥ በማጠናከር የጋራ ተጠቃሚነታቸውን ለማረጋገጥ እንደሚሰሩ ገለጹ

አዲስ አበባ፤ የካቲት 13/2016 (ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ እና ኬንያ ትብብራቸውን  ይበልጥ በማጠናከር የጋራ ተጠቃሚነታቸውን ለማረጋገጥ እንደሚሰሩ ገለጹ።

36ኛው የኢትዮ-ኬንያ  የሚኒስትሮች የጋራ ኮሚሽን ስብሰባ ለሶስት ቀናት  በአዲስ አበባ ተካሂዷል።

በስብሰባውም በውጭ ጉዳይና መከላከያ ዘርፎች፣ በንግድና ኢንቨስትመንት እንዲሁም በማህበራዊ ዘርፎች ውይይት የተደረገ ሲሆን፥ ሁለቱ ሀገራት በ7 ጉዳዮች  አብረው ለመስራት የመግባቢያ ስምምነት ተፈራርመዋል።

ስምምነቶቹ በቱሪዝም፣ ባህል ፣በዱር እንስሳት ጥበቃ፣ በትምህርት የአቅም ግንባታ ዘርፍ፣ በማረሚያ ቤት አገልግሎት፣ በዓሳ ልማትና በፔትሮሌም ዘርፎች እንደሆኑ ተገልጿል።

ስምምነቱን የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አምባሳደር ታዬ አፅቀሥላሴ እና የኬንያ ካቢኔ፣  የውጭ እና የዲያስፖራ ጉዳዮች ሚኒስትር ሙሳሊያ ሙዳቫዲ ተፈራርመዋል።


 

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አምባሳደር ታዬ አጽቀሥላሴ በዚሁ ጊዜ እንደገለጹት፣ የኢትዮጵያና ኬንያ ህዝቦች በመልክዓ- ምድር፣  በባህል፣ ቋንቋ፣ በታሪክ የተሳሰሩና ረጅም ዘመን ያስቆጠረ ወዳጅነት ያላቸው ሀገራት ናቸው። 

የአየር ንብረት ለውጥ፣ ሽብርተኝነት፣ ስራ አጥነት እና ህገወጥ ስደትን የሀገራቱ የጋራ ችግሮች እንደሆኑ ጠቅሰው፥ ችግሮቹን በጋራ ለመፍታት መስራት እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል። 

ባለፉት ሶስት ቀናት በተካሄደው የሚኒስቴሮች የጋራ ኮሚሽን ስብሰባ ሀገራቱ ትብብራቸውን አጠናክረው በሚቀጥሉባቸው ጉዳዮች ላይ ውይይት በማድረግ ስምምነት መፈረሙንም ገልፀዋል።


 

የኬንያ የካቢኔ፣ የውጭ እና የዲያስፖራ ጉዳዮች ሚኒስትር ሙሳሊያ ሙዳቫዲ በበኩላቸው፣ የሁለቱ ሀገራት በጋራ ተጠቃሚነት ላይ የተመሰረተ ወዳጅነት  ተጠናክሮ መቀጠሉን አስረድተዋል። 

ዛሬ የተፈረመው የመግባቢያ ስምምነት የሁለቱን ሀገራት ትብብር  በብዙ መስኮች ይበልጥ እንደሚያሳድገው አመላክተዋል።

ኢትዮጵያ እና ኬንያ ቀጣናዊ፣ አህጉራዊ እና ዓለም አቀፋዊ ጉዳዮች ላይ ያላቸውን ትብብር አጠናክረው እንደሚቀጥሉም ነው ሚኒስትሩ የተናገሩት።

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም