ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ ለቀጣናዊ ትስስርና ለመሰረተ ልማት ግንባታ የሰጠችው ትኩረት ቀጣይነት ያለው ጠንካራ ኢኮኖሚ ለመገንባት ያስችላታል

አዲስ አበባ፤ የካቲት 13/2016(ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ ለቀጣናዊ ትስስርና ለመሰረተ ልማት ግንባታ የሰጠችው ትኩረት ቀጣይነት ያለው ፈጣን የኢኮኖሚ እድገት ለማስመዝገብ እንደሚያስችላት ዕውቁ አሜሪካዊ የምጣኔ ሀብት ተንታኝ ፕሮፌሰር ጀፍሪ ሳክስ ገለጹ።

ፕሮፌሰሩ ኢትዮጵያ በአፍሪካ ቀንድ ቀጣና እና ከተቀረው ዓለም በንግድና ገበያ ብሎም በመሰረተ ልማት ትስስር ለመፍጠር የምታደርገውን ጥረትም አድንቀዋል።

ዕውቁ አሜሪካዊ የምጣኔ ሀብት ተንታኝ ፕሮፌሰር ጀፍሪ ሳክስ ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ፣ ኢትዮጵያ ውስጥ በሁሉም መስክ ሁለንተናዊ የልማት እምርታ እየታየ መሆኑን ተናግረዋል።

ፕሮፌሰር ሳክስ አክለውም በበርካታ የኢትዮጵያ አካባቢዎች ኢንዱስትሪ ፓርኮች፣ ባቡር እና ሌሎች መሰረተ ልማት ዝርጋታዎች በተጨባጭ እየተከናወኑ መሆኑን እንደተመለከቱ አረጋግጠዋል።

በግብርና ምርትና ምርታማነት ረገድም እየተከናወኑ ያሉ ስራዎችን ለአብነት ጠቅሰዋል።

ኢትዮጵያ ኢንቨስትመንትን ለመሳብ ካላት ቁልፍ ስትራቴጂዎቿ ባሻገር በቅርቡ የብሪክስን ጎራ መቀላቀሏ የኢንቨስትመንት እና የፋይናንስ አማራጮቿን ለማስፋት ትልቅ ዕድል እንደሚከፍት ተናግረዋል።

ብሪክስ 40 በመቶውን የዓለም ምርት የሚሸፍኑ ሀገራትን በአባልነት ያቀፈ በመሆኑ በቀጣይ ለኢትዮጵያ የሚኖረውን አውንታዊ ፋይዳ አጽንኦት ሰጥተው አብራርተዋል።

የብሪክስ አባላት ከዶላር ውጭ የሆነ ክፍያ የሚፈጸምበት የራሱ ፋይናንስ ስርዓት ለመዘርጋት ዕቅድ መያዙን አውስተው፣ የብሪክስ ኒው ዲቨሎፕመንት ባንክ ወደ ስራ መግባቱም የላቀ ፋይዳ አለው ብለዋል።

በተመሳሳይ ኢትዮጵያ ከባህረ ሰላጤው ሀገራት ጋር የፈጠረችው ጥብቅ ትስስር፥ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንትን በስፋት ለመሳብ እንደሚያስችላት ጠቁመዋል።

ከዚህ ባሻገር ኢትዮጵያ ቀጠናዊ ትስስር እንዲጎለብት ያላትን ብርቱ ጥረት አድንቀው፤ በመሰረተ ልማት ረገድ ቀጣናውን የሚያስተሳስር ብርቱ ስራ እያከናወነች ስለመሆኑ ገልጸዋል።

ይህም በአፍሪካ ቀንድ ቀጣና ሰላም እንዲሁም ዘላቂ ኢኮኖሚያዊ ትብብር እና ኢንቨስትመንትን ለማረጋገጥ ትልቅ ፋይዳ እንዳለው ነው የተናገሩት።

በአጠቃላይ ኢትዮጵያ ለቀጣናዊ ትስስር የሚበጁ መሰረተ ልማት ግንባታዎች ላይ ያደረገችው ትኩረት ቀጣይነት ያለው ፈጣን ኢኮኖሚ እድገት እንድታስመዘግብ ያደርጋታል ብለዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም