በክልሉ የማህበረሰብ አቀፍ የፖሊስ አገልግሎትን በማጠናከር ሰላምን በዘላቂነት ለማስፈን ይሰራል- አቶ እንዳሻው ጣሰው - ኢዜአ አማርኛ
በክልሉ የማህበረሰብ አቀፍ የፖሊስ አገልግሎትን በማጠናከር ሰላምን በዘላቂነት ለማስፈን ይሰራል- አቶ እንዳሻው ጣሰው
ሆሳዕና ፤የካቲት 13/2016 (ኢዜአ) ፦በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የማህበረሰብ አቀፍ የፖሊስ አገልግሎትን በማጠናከር ለክልሉ ዘላቂ ሰላም በትኩረት እንደሚሰራ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ እንዳሻው ጣሰው አስታወቁ።
የክልሉ ወቅታዊ የሰላምና የፀጥታ ሁኔታ ዛሬ በሆሳዕና ከተማ ተገምግሟል።
የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ እንዳሻው ጣሰው በዚህ ወቅት እንዳሉት በክልሉ ማህበረሰብ አቀፍ የፖሊስ አገልግሎትን ማጠናከር የፀጥታ ኃይሉን ለመደገፍና የአካባቢን ሰላም ዘላቂ ለማድረግ ወሳኝ ነው።
በመሆኑም ህብረተሰቡ የአካባቢውን ሰላም በንቃት እንዲጠብቅ በሁሉም የክልሉ አካባቢዎች ህዝቡን ባሳተፈ መልኩ ሚሊሻዎችን ለማደራጀት እንደሚሰራ ገልጸዋል።
ሁሉም ለአካባቢው ሰላም እንዲቆም በማድረግ ህገወጥ የመሳሪያ ዝውውርን ከመከላከል ባለፈ ሰላምን የሚያደፈርሱ ጉዳዮች እንዳይከሰቱ በትኩረት መስራት እንደሚገባም አቶ አንዳሻው አመልክተዋል።
አምራችና ሸማቹ በነፃነት እንዳይገበያዩ የግብይት ስርዓቱን በማወክ የግል ጥቅማቸውን የሚያሳድዱ አካላትን ተከታትሎ ለህግ ማቅረብ የሚቻለው ማህበረሰብ አቀፍ የፖሊስ አገልግሎት ሲጠናከር በመሆኑ ለዚህም ትኩረት ሰጥቶ መስራት እንደሚገባም አሳስበዋል።
በክልሉ በአንዳንድ ከተሞች የሚፈጸሙ የንጥቂያ፣ዝርፊያና ሌሎች ወንጀሎችን ክትትል ማድረግና ህጋዊ እርምጃ መውሰድ የተቀናጀ የፀጥታ ኃይሉ የመጀመሪያና በልዩ የትኩረት የሚሰራው መሆን እንዳለበት አስታውቀዋል።
የክልሉ ሰላምና ፀጥታ ቢሮ ኃላፊ አቶ ተመስገን ካሳ በበኩላቸው እንዳሉት የክልሉን ህዝብ የአብሮነት፣ የመቻቻልና የፍቅር እሴቶች ለዘላቂ ሰላም ያላቸውን አስተዋጽኦ ለማጠናከር እየተሰራ ነው ብለዋል።
የክልሉን ሰላም በዘላቂነት ለማስቀጠል ከማህበረሰቡ ጋር በቅንጅት በተሰራው ሥራ አመርቂ ውጤት መመዝገቡንም ጠቁመዋል።
የክልሉ ፀጥታ ኃይል የአካባቢውን ህብረተሰብ ሰላም ለማረጋገጥ ከወገንተኝነት በጸዳ መልኩ እየሰራ መሆኑንም አቶ ተመስገን ተናግረዋል።
የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ሽመልስ ካሳ እንደገለፁት፣ በክልሉ በተለያዩ ምክንያቶች ይከሰቱ የነበሩ ችግሮችን ከማህበረሰቡ ጋር በመተባበር የመፍታት ስራ እየተከናወነ ይገኛል።
የማህበረሰብ አቀፍ ፖሊስ አገልግሎትን ተግባራዊ በማድረግ የዜጎችን ደህንነት ይበልጥ አስተማማኝና ሰላማዊ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑንም ጠቁመዋል።
ክልሉ ፍፁም ሰላማዊ እንዲሆን ለዜጎች ሰላምና አብሮነት ልዩ ትኩረት መሰጠቱንም ነው አቶ ሽመልስ የገለፁት።
በመርሃ ግብሩ ላይ የክልሉ ከፍተኛ አመራሮች፣ የዞን አስተዳዳሪዎች እና የፖሊስ አዛዦች ተሳትፈዋል።