ቀጥታ፡

በህገ-ወጥ ምንዛሪ ተግባር የተጠረጠሩ 23 ግለሰቦችን መያዙን ፖሊስ አስታወቀ

አዲስ አበባ፤ የካቲት 13/2016(ኢዜአ)፦ከህገ ወጥ የገንዘብ ምንዛሪና ክምችት ጋር ተያይዞ በተለያዩ ክፍለ ከተሞች ባከናወነው ተግባር ከሶስት ሚሊዮን ብር በላይ፣ የተለያዩ ሃገራት ገንዘቦችና 23 ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን የአዲስ አበባ ፖሊስ ገለጸ።

የሃገርን ኢኮኖሚ ለማዳከም የሚፈፀሙ ወንጀሎችን መነሻ በማድረግ በተለይም ህገ-ወጥ የውጪ ሃገራት ገንዘብ ምንዛሪ በሚከናወንባቸው ቦታዎችና ገንዘብን ከብሄራዊ ባንክ መመሪያ ውጪ በመኖሪያ ቤታቸው በሚያከማቹ ግለሰቦች ላይ ፖሊስ መረጃ ሲያሰባስብና ጥናት ሲያደርግ መቆቱን ገልጿል።


 

ጥናቱንና የህዝብ ጥቆማን መነሻ በማድረግ ሰሞኑን በተለያዩ ክፍለ ከተሞች በተከናወነ ተግባር 3 ሚሊዮን 24 ሺህ 180 ብር፣ 20 ሺህ ሪያል ፣ 3ሺህ 758 የአሜሪካ ዶላርና የተለያዩ ሃገራት ገንዘቦች ከብሄራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ጋር በመተባበር በቁጥጥር ስር ውለዋል።

በቂርቆስ ክፍለ ከተማ ወረዳ 7 ጋንዲ ሆስፒታል አካባቢ፣ በወረዳ 2 ሸዋ ዳቦ እና መስቀል ፍላወር ተብለው በሚጠሩት አካባቢዎች በሚገኙና ከህገ ወጥ የውጪ ሃገራት ገንዘቦች ምንዛሪ ጋር በተያያዘ በጥናቱ ውስጥ በተካተቱ አራት ንግድ ቤቶች ላይ በተደረገ ብርበራ 350 ሺህ ብር ፣2ሺህ 803 የአሜሪካ ዶላር እና 20 ሺህ ሪያል ተይዟል፡፡

በተጨማሪም መስቀል ፍላወር ተብሎ በሚጠራው አካባቢ በሚገኝ አንድ ፔንሲዮን ውስጥ ብርበራ ሲደረግ በወረቀት ተጠቅልሎ ለሽያጭ የተዘጋጀ አደንዛዥ ዕፅ ተገኝቷል።

በቦሌ ክፍለ ከተማ በተለያዩ አካባቢዎች በሚገኙና የውጪ ሃገራት ገንዘቦችን በህገ ወጥ መንገድ ከመመንዘር ወንጀል ጋር ተያይዞ በጥናት በተለዩ 15 ንግድ ቤቶች ላይ በተደረገ ብርበራ የተያዘው 1ሚሊዮን 305 ሺህ ብር እና የተለያዩ ሃገራት ገንዘቦች መያዛቸውም ተገልጿል።

ፖሊስ ከብሄራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ጋር በመተባበር ባከናወነው በዚህ ተግባር ከገንዘቦቹ በተጨማሪ ሃሰተኛ ገንዘብ ለማዘጋጀት በብር መጠን ተቆርጠው የተቀመጡ ወረቀቶች፣ የነዋሪነት መታወቂያዎች፣ፓስፖርቶች እና የተለያዩ የባንክ ሰነዶች ተገኝተዋል።

ኮልፌ ቀራንዮ ክፍለ ከተማ ወረዳ 8 ልዩ ቦታው ቀራንዮ የሺ ደበሌ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ አንድ ግለሰብ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ባንክ መመሪያን በመተላለፍ በመኖሪያ ቤቱ ውስጥ የተለያዩ ሃገራት ገንዘቦችን እና የኢትዮጵያ ብር ከተፈቀደው መጠን ባላይ ስለማከማቸቱ በደረሰ ጥቆማ እና ፖሊስ ባደረገው ክትትል ሊያዝ ችሏል፡፡

በፍርድ ቤት ትዕዛዝ በተጠርጣሪው መኖሪያ ቤት ውስጥ በተከናወነ ብርበራ 955 የአሜሪካ ዶላር፣ 2 ሺህ 270 የኤርትራ ናቅፋ እና 300 ሺህ የኢትዮጵያ ብር ተገኝቷል፡፡

በተመሳሳይ በጉለሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 3 መነን አደባባይ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ በፍርድ ቤት ትዕዛዝ በግለሰብ መኖሪያ ቤት በተደረገ ብርበራ 1ሚሊዮን 69 ሺህ 180 ብር ተከማችቶ በመገኘቱ በቁጥጥር ስር ሊውል ችሏል፡፡

በአጠቃላይ 23 ተጠርጣሪዎች ተይዘው ምርመራ እየተጣራ የሚገኝ ሲሆን ህጋዊ የንግድ ሽፋንን ህገ- ወጥ ተግባር የሚፈፅሙ ግለሰቦች ከዚህ ድርጊታቸው እንዲታቀቡ ያሳሰበው ፖሊስ ህብረተሰቡም አስፈላጊውን ጥቆማ በማድረግ ትብብሩን እንዲቀጥል በማህበራዊ ትስስር ገጹ ጥሪ አቅርቧል።

 

 

 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም