ቀጥታ፡

የህብረት ስራ ማህበራት ማሻሻያ  አደረጃጀቶችን በማስተካከል የአባላትን ሃብትና ንብረት ከምዝበራና ከብክነት የሚታደግ ነው

አዲስ አበባ፤ የካቲት 13/2016 (ኢዜአ)፦የህብረት ስራ ማህበራት ማሻሻያ አደረጃጀትን በማስተካከል የአባላትን ሃብትና ንብረት ከምዝበራና ከብክነት የሚታደግ መሆኑን የኢትዮጵያ ህብረት ስራ ኮሚሽን አስታወቀ።

በኮሚሽኑ የፋይናንስ  ልማት መሪ ስራ አስፈጻሚ አቶ ብርሃኑ ዱፌራ ለኢዜአ እንደገለጹት የህብረት ስራ ማህበራት የህብረተሰቡን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች በማቃለል ለሀገር ዕድገት ከፍተኛ ድርሻ በማበርከት ላይ ናቸው፡፡ 

በኢትዮጵያ የሚገኙ የህብረት ስራ ማህበራት ባለፉት 20 ዓመታት የግብርና ምርትና ምርታማነትን በማሳደግና በግብአት አቅርቦት ዘርፍ የድርሻቸውን ለመወጣት ጥረት እያደረጉ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ከዚህ ባለፈ በግብርና ምርቶች ላይ እሴት በመጨመር ለሸማቾች ለማቅረብና የአነስተኛ ቁጠባና ብድር አገልግሎትን ተደራሽ ለማድረግ እየሰሩ ይገኛሉ፡፡

የህብረት ስራ ማኅበራት ወቅቱን የዋጀ የአሰራር፣ የአደረጃጀት እና የሰዉ ሀይል እንዲኖራቸው የሚረዳ የመዋቅር ማሻሻያ (ሪፎርም) እየተካሄደ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ማሻሻያው በዋነኝነት መሰረታዊ፣ ዩኒዬንና ፌዴሬሽን በሚል የሚታወቁ አደረጃጀቶችን ለማስተካከል ቅድሚያ የተሰጠው መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

እነዚህ አደረጃጀቶች በተመሳሳይ ደረጃና ወጥ አደረጃጀት በድጋሜ ተመስርተው ወደ ተግባር እንዲገቡ ለማስቻል ማስተካከያ ማስፈለጉን ገልጸዋል፡፡

በአዲሱ አደረጃጀት በባህሪ የሚመሳሰሉትን እንዲዋሃዱ በማድረግና ሃብታቸውን በማሳደግ አባላቶቻቸው ተጠቃሚ የሚሆኑበት አሰራር ተግባራዊ እየተደረገ መሆኑን አስታውቀዋል።

ማህበራቱ ዘመናዊ ግብይትና ቴክኖሎጂን እንዲጠቀሙ ለማስቻልና በሰለጠነ ባለሙያ እንዲመሩ ዕድል የሚፈጠር ማሻሻያ ተግባራዊ በመደረግ ላይ እንደሚገኝም አስረድተዋል፡፡

በተጨማሪ ዘመናዊ የፋይናንስ አስተዳደርና አመራርን ተግባራዊ ማድረግ በሪፎርሙ ትኩረት የተሰጠው ነው ብለዋል፡፡

ይህም የህብረት ስራ ማህበራት ባንክና ኢንሹራንስ በማቋቋም ወደ ተግባር እንዲገቡ የሚያግዝ ከመሆኑ ባሻገር የቁጥጥር ስርዓቱን በማጠናከር የአባላትን ሃብትና ንብረት ከምዝበራና ከብክነት የሚታደግ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት ማሻሻያውን በተመለከተ በቂ ግንዛቤና መግባባት መፈጠሩን ጠቅሰው የድሬደዋ ከተማ አስተዳደርና የኦሮሚያ ክልል ወደ ስራ መግባታቸውን ገልጸዋል፡፡

ክልሎች ማሻሻያውን ከማድረጋቸው በፊት መረጃ ማጥራትና ማረጋገጥ ፣አደረጃጃትን ማስተካከል ፣ ተመሳሳይ ባህርይና ደረጃ ያላቸውን ማዋሃድ እንደሚጠበቅባቸው ተናግረዋል፡፡

እንደዚሁም ማህበራቱን በደረጃ ማስቀመጥና የእውቅና ማረጋገጫቸውን ማደስ ቅድሚያ የሚሰጣቸው ተግባራት መሆናቸውን ጠቅሰዋል፡፡

ማሻሻያው የህብረት ስራ ማህበራት የማህበረሰቡን ህይወት ለማሻሻልና ለሀገር ኢኮኖሚ ግንባታ የበኩላቸዉን አስተዋጽኦ እንዲያበረክቱ የሚያስችል አላማ ያለው መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም