የኢትዮጵያ አረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር በአየር ንብረት ለውጥ ክፉኛ እየተፈተነች ላለችው አፍሪካ ሁነኛ መፍትሔ ነው- የተባበሩት መንግስታት የአካባቢ ጥበቃ ፕሮግራም - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ አረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር በአየር ንብረት ለውጥ ክፉኛ እየተፈተነች ላለችው አፍሪካ ሁነኛ መፍትሔ ነው- የተባበሩት መንግስታት የአካባቢ ጥበቃ ፕሮግራም
አዲስ አበባ፤ የካቲት 13/2016 (ኢዜአ)፦የኢትዮጵያ አረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር በበረሃማነት መስፋፋት እና በአየር ንብረት ለውጥ ክፉኛ እየተፈተነች ለምትገኘው አፍሪካ ሁነኛ መፍትሔ እንደሆነ በተበባሩት መንግስታት የአካባቢ ጥበቃ ፕሮግራም ዋና ዳይሬክተር ኢንገር አንደርሰን ተናገሩ።
በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አነሳሽነት በ2011 ዓ.ም ተግባራዊ መሆን በጀመረው የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር እስካሁን 32 ነጥብ 5 ቢሊዮን ችግኞች ተተክለዋል።
በተባበሩት መንግስታት የአካባቢ ጥበቃ ፕሮግራም ዋና ዳይሬክተር ኢንገር አንደርሰን ለኢዜአ እንዳሉት፤ የአየር ንብረት ለውጥ ዓለምን ክፉኛ እየፈተነ ነው።
በተለይም ለአየር ንብረት ለውጥ መዛባት እምብዛም አበርክቶ የሌላት አፍሪካ፥ በበርሃማነት መስፋፋት እና አካባቢ ብክለት ቀውሶች ክፉኛ ገፈት ቀማሽ መሆኗን ገልጸዋል።
የአፈር ለምነትን በመቀነስ በአህጉሪቱ የግብርና ምርትና ምርታማነት ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ እያሳደረ ስለመምጣቱ አንስተዋል።
ከዚህ አኳያ ድርጅታቸው ኢትዮጵያን ጨምሮ አፍሪካውያን ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር ፖሊሲ እንዲከተሉ ከመደገፍ ባሻገር ለሚደርስባቸው ተጽዕኖ ተመጣጣኝ የፋይናንስ ድጋፍ እያደረገ ነው ብለዋል።
በዓለም አየር ንብረት ለውጥ ጉባዔ የተወሰነው የአየር ንብረት ለውጥ የጉዳት ካሳን ገቢራዊ ለማድረግ ድርጅታቸው በቢሊዮኖች የሚገመት ገንዘብ እንደሚያስፈልገው ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖን ለመቀነስና በዘላቂነት ለመከላከል እያደረገች ያለውን ጥረት አድንቀው፣ "ኢትዮጵያ አረንጓዴ አሻራን በመተግበሯ ደስተኞች ነን" ብለዋል።
የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር የአፈር ለምነትን በመጨመር ለግብርናው ዘርፍና ለአካባቢ ስርዓተ ምህዳር መጠበቅ ፋይዳው የጎላ መሆኑን ጠቅሰዋል።
ይህ ከተባበሩት መንግስታት የአካባቢ ጥበቃ ፕሮግራም ጋር የሚጣጣመው የኢትዮጵያ ኢኒሼቲቭ፥ አፍሪካውያን እያጋጠማቸው ያለውን የአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖ ለመቀነስ ሁነኛ መፍትሔ ነው ብለዋል።
የአረንጓዴ አሻራና መሰል የአካባቢ ጥበቃ መርሐ ግብሮችን ማስፋፋት ለዓለም ኢኮኖሚ እምርታ አይተኬ ሚና እንዳላቸውም አረጋግጠዋል።
ኦክስፋም በ2021 ባወጣው መረጃ ወደ ከባቢ አየር ከሚለቀቀው ካርበን ውስጥ ከ50 በመቶ በላይ የሚመነጨው ከዓለም ህዝብ 10 በመቶ የሚሆኑ ሀብታሞች ከሚቆጣጠሯቸው ኢንዱስትሪዎች ነው።
በአንጻሩ 17 በመቶ የዓለም ህዝብ የሚገኝባት አፍሪካ በካርበን ልቀት ያላት ድርሻ 4 በመቶ ብቻ ነው።
በዚህም በዓለም ላይ በአየር ንብረት ለውጥ ጉዳት ከሚያስተናግዱ 10 ሀገራት 7ቱ በአፍሪካ እንደሚገኙ የዓለም አቀፉ የነብስ አደን ኮሚቴ መረጃ ያሳያል።