ኢትዮጵያን በምስራቅ አፍሪካ የሎጂስቲክስ አገልግሎት መሪ የሚያደርግ አቅም እየፈጠርን ነው - የኢትዮጵያ ባሕር ትራንስፖርት እና ሎጂስቲክስ - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያን በምስራቅ አፍሪካ የሎጂስቲክስ አገልግሎት መሪ የሚያደርግ አቅም እየፈጠርን ነው - የኢትዮጵያ ባሕር ትራንስፖርት እና ሎጂስቲክስ
አዲስ አበባ፤ የካቲት 13/2016(ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያን በምስራቅ አፍሪካ የሎጂስቲክስ አገልግሎት መሪ የሚያደርግ ተጨባጭ አቅም እየተፈጠረ መሆኑን የኢትዮጵያ ባሕር ትራንስፖርት እና ሎጂስቲክስ ዋና ስራ አስፈፃሚው በሪሶ አመሎ (ዶ/ር) ተናገሩ።
ዋና ስራ አስፈፃሚው ለኢዜአ እንደገለጹት፥ ተቋሙ ባለፉት ስድስት ወራት 400 ሺህ ቶን የገቢና ወጪ እቃዎችን በማጓጓዝ ከ27 ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ አግኝቷል።
የኢትዮጵያ ባህር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሀገራዊ የኢኮኖሚ እድገትንና የህዝብን አዳጊ ፍላጎት ታሳቢ ያደረገ ለውጥ እያካሄደ መሆኑንም ተናግረዋል።
በዚህም ተጨባጭ ውጤት እያመጣ መሆኑን ጠቅሰው፥ ለአብነት በገቢ ረገድ ባለፉት ስድስት ወራት 17 ቢሊዮን ብር ለመሰብሰብ አቅዶ፥ 27 ቢሊዮን ብር ገቢ ማስመዝገቡን አንስተዋል።
ከዚህ ውስጥ 3 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር ትርፍ እንዳገኘም ነው የጠቀሱት።
መንግሥት ባለፉት አምስት ዓመታት ለድርጅቱ መሻሻል ከፍተኛ ትኩረት መስጠቱን ያነሱት ዋና ስራ አስፈጻሚው፥ በዚህም ኢትዮጵያን በምስራቅ አፍሪካ ግዙፉ የሎጂስቲክስ አገልግሎት ባለቤት ለማድረግ አቅም እየፈጠርን ነው ብለዋል።
የኢትዮጵያ የባህር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ መዳረሻዎችን በማስፋትና የደንበኞችን ቁጥር በማሳደግ ውጤታማ ስራዎችን በማከናወን ላይ እንደሚገኝም አንስተዋል።
በዓለም አቀፍ ደረጃም ተወዳዳሪና ተመራጭ የባሕር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ድርጅት ለመሆን ጉዞ ጀምረናል ነው ያሉት።
ድርጅቱ ባለፉት ስድስት ወራት ውስጥ ከ400 ሺህ ቶን በላይ የወጪና ገቢ እቃዎችን ያጓጓዘ ሲሆን፤ ከባለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸርም ከፍተኛ ጭማሪ እንዳለው ጠቅሰዋል።
ይህም ድርጅቱ ለሀገር እድገት ከፍተኛ ተሳትፎ እያደረገ መሆኑን እንደሚያሳይ በማንሳት፥ በቀጣይም ቀልጣፋ አገልግሎት በመስጠት የሀገርን ግብ እውን ለማድረግ የበኩሉን እንደሚወጣ ገልጸዋል።
በባሕር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ መስኩ ላይ ለመሳተፍ ለሚፈልጉ ባለሃብቶች ሰፊ እድል መኖሩንም ጠቁመዋል።