ኢትዮጵያ እና ኬንያ በተለያዩ መስኮች ላይ በትብብር መስራት የሚያስችላቸውን ስምምነት ተፈራረሙ - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ እና ኬንያ በተለያዩ መስኮች ላይ በትብብር መስራት የሚያስችላቸውን ስምምነት ተፈራረሙ
አዲስ አበባ፤ የካቲት 13/2016(ኢዜአ)፦ኢትዮጵያና ኬንያ ፖለቲካና ደህንነትን ጨምሮ በተለያዩ ዘርፎች መስራት የሚያስችላቸውን የጋራ መግባቢያ ስምምነት ዛሬ ተፈራርመዋል።
ኢትዮጵያና ኬንያ በሰባት መስኮች ላይ በጋራ መስራት የሚያስችላቸውን ስምምነት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አምባሳደር ታዬ አፅቀሥላሴ እና የኬንያ የውጭ ጉዳይ እና የዲያስፖራ ጉዳዮች የካቢኔ ፀሐፊ ሙሳሊያ ሙዳቫዲ ተፈራርመዋል።
ስምምነቱ በፖለቲካ እና ደህንነት፣ በቱሪዝም፣ በባህል ፣ በ”ብሉ ኢኮኖሚ”፣ በግብርናና አሳ ሀብት ፣ በዱር እንስሳት ጥበቃ፣ በፐብሊክ ሰርቪስና አቅም ግንባታ ጉዳዮች ሁለቱ ሀገራት በጋራ መስራት የሚያስችላቸው ነው።
በስምምነቱ ላይ ሁለቱ ሀገራት ያላቸውን ታሪካዊና ባህላዊ ትስስር በተለያዩ መስኮች ይበልጥ ለማጠናከር እንደሚሰራ ተገልጿል።
ኢትዮጵያና ኬንያ ከዚህም ቀደም ቀጣናዊ ትብብር፣ ንግድና ኢነርጂን ጨምሮ በበርካታ መስኮች በትብብር መስራት የሚያስችሏቸውን ስምምነቶች መፈራረማቸው ይታወሳል።
እ.አ.አ በ2022 ኢትዮጵያ ለኬንያ የኤሌክትሪክ ኃይል ለመሸጥ የተፈራረመችው ስምምነት ተጠቃሽ ነው።