ቀጥታ፡

አባቶች በአድዋ ከሰሩት አኩሪ ገድል በመማር ትውልዱ የጋራ ታሪኩንና አንድነቱን ሊጠብቅ ይገባል- የአዳማ ከተማ የአገር ሽማግሌዎች

አዳማ፤የካቲት 13/2016 (ኢዜአ)፦ አባቶች በአድዋ ከሰሩት አኩሪ ገድል በመማር ትውልዱ የጋራ ታሪኩንና አንድነቱን ሊጠብቅ ይገባል ሲሉ ኢዜአ ያነጋገራቸው የአዳማ ከተማ የአገር ሽማግሌዎች ገለጹ።

በአዲስ አበባ የተገነባው የአድዋ ድል መታሰቢያ ሙዚየም ኢትዮጵያውያን የጋራ ታሪካቸውን የሚጠብቁበትና የሚንከባከቡበት እድል የፈጠረ መሆኑን ሰሞኑን በተለያየ መልኩ እየተገለጸ ነው።

ኢዜአ ይህንኑ መነሻ በማድረግ ከአዳማ ከተማ የአገር ሽማግሌዎች ጋር ቆይታ አድርጓል።

የአዳማ ከተማ የሀገር ሽማግሌዎች ጉባዔ ምክትል ሰብሳቢ አቶ ፈይሳ መገርሳ እንደገለፁት "አድዋ የኢትዮጵያውያን የአንድነትና የጋራ ማንነት ምልክት ነው"።

የአድዋ ሙዝየም የኢትዮጵያ ህዝቦች የነበራቸውን ገድልና የጋራ ታሪካቸውን በአግባቡ እንዲገነዘቡና አጉልተው ለማሳየት የሚያስችል መሆኑንም ተናግረዋል።

''ትውልዱ ከዚህ ብዙ ነገር ይማራል'' ያሉት አቶ ፈይሳ፤ ድሉ አባቶች ጠላትን ድል አድርገው የሀገር ሉዓላዊነትና የህዝቦችን ነፃነት ያስከበሩበት ገድል ነው ብለዋል።

''የአድዋ ድል መታሰቢያ ሙዚየም የኢትዮጵያዊያን የጋራ አንድነት ምልክት መሆኑን ብሔር ብሔረሰቦች እንዲገነዘቡ በር የከፈተ ሙዝየም ነው'' ነው ሲሉም ገልጸዋል።

''በወቅቱ ጠላትን ድል አድርገን እስከ ዛሬ በነፃነት ኖረናል፤ አሁንም ህዝቡ በአንድነት በመቆም ታሪኩን መድገም አለበት'' ያሉት የአገር ሽማግሌው፤ ''እርስ በራሳችን መጋጨት አቁመን የአገራችን አንድነት ማስቀጠል አለብን'' ብለዋል።

የአሁኑ ትውልድ የአንድነት ምልክት ከሆነው አድዋ በመማር አገሩን ወደ ፊት ማስቀጠል አለበት ብለዋል።

አድዋ በየዓመቱ  የሚዘከር ቢሆንም ትውልዱ የአባቶችን ገድልና የጋራ ታሪክ የሚዘክርበት፣ የተሻለ ነፃነት፣ አንድነትና ጀግንነት የሚማርበት ምልክት እንዳልነበረው ያስታወሱት ደግሞ ሌላው የአገር ሽማግሌ አቶ ግርማ ሰንበቶ ናቸው።

የአድዋ ሙዝየም ይሄንን ጥያቄ የመለሰ ከመሆኑም ባለፈ አሁን ያለው ትውልድ የአባቶቹን ፈለግ በመከተል ከእሱ የሚጠበቅበትን በአንድነት እንዲወጣ ያነሳሳል ብለዋል።

ትውልዱ ከአባቶቹ አንድነትን እንዲማር፣ በፖለቲካ አስተሳሰብና በብሔር ሳይከፋፈል ችግሮችን በውይይት፣ በምክክርና በመተራረም እንዲፈታና የተሻለ አገር እንዲገነባ የሚያነሳሳ መሆኑን በማከል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም