ቀጥታ፡

የአፍሪካ ሕብረት የፓን አፍሪካ የእንስሳት ክትባት ቤተ- ሙከራ ሕንጻ ግንባታ የመሰረተ ድንጋይ ተቀመጠ

አዲስ አበባ፤ የካቲት 13/2016 (ኢዜአ)፦ የአፍሪካ ሕብረት የፓን አፍሪካ እንስሳት ክትባት የቤተ- ሙከራ ሕንጻ ግንባታ ፕሮጀክት የመሰረተ ድንጋይ ተቀመጠ።

የአፍሪካ ሕብረት ኮሚሽን ሊቀ መንበር ሙሳ ፋኪ ማህማት በቢሾፍቱ ከተማ ለሚገነባው የአፍሪካ ህብረት የፓን አፍሪካ የእንስሳት ክትባት የቤተ ሙከራ የመሰረት ድንጋይ አስቀምጠዋል።

በስነ- ስርዓቱ ላይ የአፍሪካ ኅብረት የግብርና፣ የገጠር ልማት፣ የብሉ ኢኮኖሚና የዘላቂ አካባቢ ኮሚሽነር አምባሳደር ጆሴፋ ሳኮ፣ የግብርና ሚኒስትር ዶክተር ግርማ አመንቴ፣ የአሜሪካ የመከላከያ ስጋት ቅነሳ ኤጀንሲ ዳይሬክተር ዶክተር ሮበርት ፖፕ እና ሌሎች ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።

በቢሾፍቱ የሚገነባው አዲስ የእንስሳት ክትባት የቤተ - ሙከራ ሕንጻ እ.አ.አ በ2004 በተቋቋመው የአፍሪካ ሕብረት የፓን አፍሪካ የእንስሳት ክትባት ማዕከል ውስጥ የሚገኝ ነው።

ግንባታው በ 3 ነጥብ 9 ሄክታር መሬት ላይ የሚያርፍና  ከ 56 ሚሊዮን ዶላር በላይ በሚሆን ወጪ የሚገነባ መሆኑ ታውቋል።

ሕንጻው በአሜሪካ የመከላከያ ስጋት ቅነሳ  ኤጀንሲ ሙሉ ድጋፍ እንደሚገነባና  ሶስት ዓመታትን የሚፈጅ መሆኑ ተገልጿል።

ቤተ- ሙከራው የአፍሪካ ሕብረት የፓን አፍሪካ የእንስሳት ክትባት ማዕከል ዓለም አቀፍ ደረጃውን እንዲያሟላና የተሰጡትን ተልዕኮዎች በአግባቡ ለመወጣት ያስችለዋል ተብሏል።

ማዕከሉ በአፍሪካ ሕብረት ኮሚሽን  የግብርና፣ የገጠር ልማት፣ ”ብሉ ኢኮኖሚ” እና ዘላቂ ከባቢ አየር የስራ ክፍል ውስጥ የሚገኝ ልዩ የቴክኒክ ቢሮ ነው።

ማዕከሉ በእንስሳት ላይ የሚደርሱ በሽታዎች እንዲሁም በሰውና በእንስሳት መካከል የሚተላለፉ በሽታዎችን መከላከል ላይ የሚሰራ ነው።

 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም