የጋምቤላ ክልል ምክር ቤት የወጡ ህጎች በአግባቡ ስራ ላይ ስለመዋላቸው ክትትልና ቁጥጥር አድርጓል - ዋና አፈ ጉባዔ - ኢዜአ አማርኛ
የጋምቤላ ክልል ምክር ቤት የወጡ ህጎች በአግባቡ ስራ ላይ ስለመዋላቸው ክትትልና ቁጥጥር አድርጓል - ዋና አፈ ጉባዔ
ጋምቤላ፤ የካቲት 13/2016(ኢዜአ)፦ ምክር ቤቱ አዳዲስ አዋጆችን ከማውጣት ባለፈ የወጡ ህጎች በአግባቡ ስራ ላይ ስለመዋላቸው ክትትልና ቁጥጥር ማድረጉን የጋምቤላ ክልል ምክርቤት አፈ-ጉባኤ ገለጹ።
የክልሉ ምክር ቤት 6ኛ ዓመት 3ኛ የስራ ዘመን 5ኛ መደበኛ ጉባዔውን ዛሬ በጋምቤላ ከተማ ማካሄድ ጀምሯል።
የምክር ቤቱ አፈ-ጉባኤ ወይዘሮ ባንቻየሁ ድንገታ ጉባዔውን ሲከፍቱ እንደገለጹት ምክር ቤቱ ባለፉት ስድስት ወራት በክልሉ የታቀዱ የልማትና የመልካም አስተዳደር ስራዎች በተያዘላቸው ጊዜ ለመፈጸማቸው የክትትልና ቁጥጥር ስራዎችን መስራቱንና የተሻለ ውጤት ማስመዝገቡን ተናግረዋል።
ምክር ቤቱ የወቅቱን ነባራዊ ሁኔታ ባገናዘበ መልኩ አዳዲስ አዋጆችን ከማውጣት ባለፈ የወጡ ህጎች በአግባቡ ስራ ላይ መዋላቸው ጭምር እየተከታተለ የእርምት እርምጃዎችን እየወሰደ መቆየቱንም ገልጸዋል።
ጉባዔው ከዛሬ ጀምሮ በሚኖረው የሁለት ቀናት ቆይታ ያለፈውን ግማሽ በጀት ዓመት የልማትና የመልካም አስተዳደር፣ የጠቅላይ ፍርድ ቤትና የዋና ኦዲተር መስሪያ ቤት የእቅድ ክንውን ሪፖርትን አድምጦ እንደሚያጸድቅ ይጠበቃል።
በተጨማሪም የቀጣይ ግማሽ በጀት ዓመት የተከለሰ የልማትና የመልካም አስተዳደር ዕቅድ፣ ረቂቅ አዋጅና ሌሎች ጉዳዮች ላይ ውይይት በማድረግ ውሳኔዎች እንደሚያሳልፍ ከወጣው የድርጊት መረሃ ግብር ለማወቅ ተችሏል።
በጉባዔው ላይ የጉባዔ አባላትን ጨምሮ የክልል፣ የዞን፣ የወረዳ አመራር አካላት፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ የሃይማኖት አባቶች፣ የወጣቶችና የሴቶች አደረጃጀትና ሌሎችም በመሳተፍ ላይ ናቸው።