ቀጥታ፡

በደቡብ ወሎ ዞን የአፈር ማዳበሪያ እየተሰራጨ ነው

ደሴ ፤ የካቲት 13/2016(ኢዜአ)፦  በአማራ ክልል በደቡብ ወሎ ዞን ለቀጣዩ መኸር ወቅት ሰብል ልማት ጥቅም ላይ የሚውል ከ200 ሺህ ኩንታል የሚበልጥ የአፈር ማዳበሪያ ለወረዳዎች መሰራጨቱን የዞኑ ግብርና መምሪያ አስታወቀ፡፡

የዞኑ ግብርና የመምሪያ ኃላፊ አቶ አህመድ ጋሎ ለኢዜአ እንደገለጹት፣ በዞኑ በ2016/17 የመኸር ወቅት የሚለማው ከ430 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት ሲሆን ለዚህም ከ500 ሺህ ኩንታል በላይ የአፈር ማዳበሪያ ያስፈልጋል፡፡

አርሶ አደሩ ለመኽር ወቅቱ የሚሆነው የአፈር ማዳበሪያ ከታህሳስ 2016 ዓ.ም ጀምሮ እየቀረበ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በተለይም ከአፈር ማዳበሪያ አቅርቦት ጋር በተያያዘ ባለፈው የመኽር ወቅት አጋጥሞ በነበረው እጥረት አርሶ አደሩን ለችግር መዳረጉን አስታውሰው፤ ይህም በምርታማነት ላይ ጫና እንዳሳደረ ተናግረዋል።


 

ዘንድሮም መሰል ችግር እንዳያጋጥም ልዩ ትኩረት በመስጠት በፍጥነት እንዲገባ በመደረጉ እስካሁን ከ310 ሺህ ኩንታል በላይ አፈር ማዳበሪያ ወደ ዞኑ መድረሱን ተናግረዋል፡፡

ከገባው ማዳበሪያ ውስጥ ከ200 ሺህ ኩንታል የሚበልጠውን በወረዳዎች ማሰራጨት የተቻለ ሲሆን፤ ከ90 ሺህ ኩንታል የሚበልጠው ደግሞ ለአርሶ አደሮች መከፋፈሉን ገልፀዋል።

ባለፈው ዓመት "በተመሳሳይ ወቅት ምንም ዓይነት ማዳበሪያ ወደ ዞኑ አልገባም ነበር" ያሉት ኃላፊው፤ ዘንድሮ ቀድሞ መግባቱ አርሶ አደሩ ተረጋግቶ የግብርና ስራውን እንዲያከናውን ምቹ ሁኔታ መፍጠሩን አመልክተዋል።

መንግስት የማዳበሪያ አቅርቦት እጥረትን ለመፍታት ቀድሞ ሥራዎችን ማጠናቀቅ መቻሉን ጠቅሰው፤ አርሶ አደሩ የማዳበሪያ አቅርቦት ችግር አለመኖሩን በመገንዘብ ከአጭበርባሪዎች እራሱን እንዲጠብቅ አሳስበዋል።

በዞኑ ጃማ ወረዳ የ09 ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር ካሳ ያሲን በሰጡት አስተያየት፤ ለቀጣዩ መኸር ዘጠኝ ኩንታል ማዳበሪያ የሚፈልጉ ሲሆን፤ እስካሁን አራት ኩንታል ማዳበሪያ መግዛታቸውን  ገልፀዋል።

የአፈር ማዳበሪያውን ቀድመው ማግኘት በመቻላቸው ተረጋግተው የግብርና  ስራቸውን በማከናወን ላይ መሆናቸውን ጠቁመዋል።

በቀጣዩ የመኸር ወቅት ሁለት ሄክታር ተኩል መሬት ስንዴ፣ ጤፍ፣ ገብስና ባቄላ ለማልማት ማቀዳቸውንም ተናግረዋል፡፡

''ዘንድሮ ማዳበሪያ ቀድሞ እየገባ በመሆኑ እንደ ባለፈው ዓመት ችግር አይገጥመንም የሚል ተስፋ አድርገናል'' ያሉት ደግሞ በተሁለደሬ ወረዳ የ08 ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር ሰይድ አብዱ ናቸው፡፡

እርሳቸው ከሚፈልጉት አራት ኩንታል ማዳበሪያ እስካሁን አንድ ኩንታል ማግኘታቸውን ጠቁመው፤ ቀሪው ደግሞ በሂደት ላይ መሆኑን ገልፀዋል።

በደቡብ ወሎ ዞን ባለፈው ዓመት ከ320 ሺህ ኩንታል በላይ የአፈር ማዳበሪያ ለአርሶ አደሩ በማሰራጨት ጥቅም ላይ እንዲውል መደረጉ ታውቋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም