በአፍሪካ ሕብረት ጉባኤ የታየው ስኬት የጸጥታና ደኅንነት መዋቅሩ ተጨባጭ ለውጥ ማድረጉን ያረጋገጠ ነው - የፀጥታና ደኅንነት የጋራ ግብረ-ኃይል - ኢዜአ አማርኛ
በአፍሪካ ሕብረት ጉባኤ የታየው ስኬት የጸጥታና ደኅንነት መዋቅሩ ተጨባጭ ለውጥ ማድረጉን ያረጋገጠ ነው - የፀጥታና ደኅንነት የጋራ ግብረ-ኃይል
አዲስ አበባ፤ የካቲት 12/2016(ኢዜአ)፦ በ37ኛው የአፍሪካ ሕብረት ጉባኤ የታየው ስኬት የጸጥታና ደኅንነት መዋቅሩ ተጨባጭ ለውጥ ማድረጉን ያረጋገጠ መሆኑን የፀጥታና ደኅንነት የጋራ ግብረ-ኃይል አስታወቀ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ለጉባዔው ስኬታማነት ሲያደርጉ የነበረው ከፍተኛ ክትትል ኢትዮጵያ በሁሉም መስክ በጉባኤው ከፍ ብላ እንድትታይ ማስቻሉንም ገልጿል።
ኢትዮጵያ በጉባኤው ለመሳተፍ የመጡ ከ8 ሺህ በላይ እንግዶችን በከብርና በአስተማማኝ ፀጥታ አስተናግዳ መሸኘቷንም ነው የገለጸው።
የፀጥታና ደኅንነት የጋራ ግብረ-ኃይልና የአፍሪካ ሕብረት ጉባዔ ዝግጅት ብሔራዊ ኮሚቴ ጉባዔውን በተመለከተ ግምገማ አካሂደዋል።
የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ጄኔራል ደመላሽ ገብረሚካኤል፥ በጉባኤው የ31 አገራት መሪዎች የ6 አገራት ምክትል መሪዎችን ጭምሮ በአጠቃላይ የ49 ሀገራት ከፍተኛ ልዑካንና የ15 ዓለም አቀፍ ተቋማት ተወካዮችና የጉባኤው ተሳታፊ እንግዶች አስተማማኝ የፀጥታና ደኅንነት ጥበቃ እንደተደረገላቸው ገልጸዋል።
ለጉባኤው ስኬታማነት ኅብረተሰቡ ዓይንና ጆሮ ሆኖ ከጸጥታ አካላት ጋር በመስራቱ ባለፉት ስምንት ቀናት አንድም ወንጀል እንዳልተፈጸመ ተናግረዋል።
ይህም ኅብረተሰቡን ያሳተፈ የወንጀል መከላከልና መቆጣጠር ሥራ ውጤት መሆኑን ነው የገለጹት።
የፀጥታና ደኅንነት ተቋማት የፅንፈኛ ኃይሎችና የአልሸባብን ሥጋት አስቀድሞ በማምከን ጉባኤው በአስተማማኝ ሁኔታ እንዲጠናቀቅ ማድረጋቸውን ገልጸዋል።
በጉባኤው ወቅት ሁከት ሊፈጥሩ የሞከሩ 33 ግለሰቦች በቁጥጥር ሥር ውለው ከጉባኤው በኋላ ወደ አገራቸው እንዲመለሱ ተደርጓል ብለዋል።
አህጉራዊ ጉባኤው ያለምንም የፀጥታ ችግር እንዲጠናቀቅ መደረጉም ኢትዮጵያ በሁሉም መስክ ታላቅነቷን ያስመሰከረችበት በመሆኑ በቀጣይም አጠናክረን እንቀጥላለን ነው ያሉት።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ብርቱካን አያኖ፥ ለመሪዎችና ለሥራ አስፈጻሚ ምክር ቤት ጉባኤ በቂ ዝግጅት በማድረግና በአግባቡ በማስተናገድ እንግዶች በሰላም መሸኘታቸውን ጠቅሰዋል።
ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ጀምሮ ከፍተኛ ክትትል ሲያደርጉ እንደነበር ጠቅሰው በዚህም ኢትዮጵያ ጉባኤው ከፍ ብላ እንድትታይ ማድረግ መቻሉን ገልጸዋል።
በአጠቃላይ ከ8 ሺህ በላይ እንግዶችን በአስተማማኝ ፀጥታና በኢትዮጵያዊ እንግዳ ተቀባይነት አስተናግደናል ብለዋል።
ለዚህ ስኬት የፀጥታና ደህንነት ተቋማት ሚና የላቀ መሆኑን ጠቅሰው፥ ኢትዮጵያ ዳግም ቀና ማለቷንና አህጉራዊ ሚናዋን በላቀ ሁኔታ እንደምትወጣ በሚገባ ማሳየቷን ተናግረዋል።
ጉባዔው አፍሪካውያን የኮሩበትና ኢትዮጵያ በእርግጥም ትልቅ አቅም እንዳላት የመሰከሩበት ሁነት ሆኖ ማለፉን ጠቁመዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከሀገር አድማስ የተሻገረ አጀንዳ ያንፀባረቁበት፣ የሀገርን ብሔራዊ ጥቅም የሚያስጠብቅ የሁለትዮሽና የባለብዙ ወገን ውይይቶችና ስምምነቶች ያደረጉበት መሆኑንም አስታውሰዋል።
ኢትዮጵያ ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ የሰራቻቸው ሥራዎች፣ በከተማ ውበት ያከናወነቻቸው ተግባራት፣ በጸጥታና ደህንነት ዘርፍ የፈጠረችው አቅም፣ በታሪክ አስቀጣይነት የሰራቻቸው ስራዎች ልምድ የተቀሰመባቸው በአጠቃላይ በጉባኤው ኢትዮጵያ ተከብራና ከፍ ብላ ታይታበታለች ብለዋል።
የብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ምክትል ዳይሬክተር ጄኔራል ሲሳይ ቶላ፥ ጉባኤው ያለምንም የፀጥታ ችግር መጠናቀቁ መንግሥት በፀጥታ ተቋማት ያካሄደው ሪፎርም ውጤት መሆኑን ተናግረዋል።
ጠንካራ የፀጥታና ደህንነት ተቋማት እየተገነቡ ስለመሆናቸው ማሳያ መሆኑን በማንሳት፤ስጋቶችን አስቀድሞ በመተንተን ለጉባኤው ተሳታፊዎች ደህንነት መጠበቅ የተሰራው ስራ ውጤት ማስገኘቱንም ጠቅሰዋል።
የሪፐብሊኩ ጥበቃ ኃይል ዋና አዛዥ ሜጀር ጄነራል አብድሮ ከድር፥ የአፍሪካ ኅብረት ጉባዔ በስኬት እንዲጠናቀቅ ከመሪዎች ጀምሮ እስከ ፍጻሜ የነበረው ከፍተኛ መናበብ ትልቅ ሚና ነበረው ብለዋል።
የፀጥታና ደህንነት ተቋማት አባላት፣ የፖለቲካና አስተዳደራዊ ተቋማት ባለሙያዎችና ህዝቡ ላደረገው አስተዋፅኦ ምስጋና አቅርበዋል።
ሁሉም የፀጥታና ደህንነት አባላት በከፍተኛ ዲሲፕሊን የደረሰባቸውን ትንኮሳ ጭምር በሥነ-ምግባር በማለፍ ለጉባኤው ስኬት ከፍተኛ አስተዋፅኦ አበርክተዋል ብለዋል።