ቀጥታ፡

በክልሉ በመሰረተ ልማት ፕሮጀክቶች አፈጻጸም ላይ ያሉ ተግዳሮቶችን ለመፍታት አመራሩ በቁርጠኝነት መስራት እንዳለበት ተገለጸ 

ሆሳዕና፤ የካቲት 12/2016 (ኢዜአ)፦ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በመሰረተ ልማት ፕሮጀክቶች አፈጻጸም ላይ የሚስተዋሉ ተግዳሮቶችን ለመፍታት በየደረጃው ያለው አመራር በቁርጠኝነት መስራት እንዳለበት ተገለጸ።

የክልሉ መንግስት የ2016 በጀት ዓመት የመጀመሪያ ስድስት ወራት የተከናወኑ የመሰረተ ልማት ሥራዎች አፈጻጸም ላይ ዛሬ በሆሳዕና ከተማ መክሯል።

በመድረኩ ላይ ከረዥም ዓመታት በፊት ሥራቸው ተጀምሮ ያልተጠናቀቁ እንዲሁም የካሳ ክፍያ በወቅቱ ባለመፈፀሙ ምክንያት የተጓተቱ የልማት ፕሮጀክቶች በህብረተሰቡ ተጠቃሚነት ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ እያሳደሩ መሆኑ ተገልጿል።

በተጨማሪም በአዲስ መልክ ግንባታቸው መጀመር ሲኖርበት ያልተጀመሩ የመንገድና የንጹህ መጠጥ ውሃ ፕሮጀክቶች ግንባታ ሂደት መዘግየቱ ሌላው በመድረኩ የተነሳ ነው።

ከመድረኩ ተሳታፊዎች መካከል የስልጤ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አሊ ከድር እንዳሉት፣ በዞኑ ከ2010 ዓ.ም ጀምሮ በገጠር ተደራሽ መንገድ መርሃ ግብር 12 የመንገድ ፕሮጀክቶች መገንባታቸውን ገልጸዋል።


 

መንገዶች ቢሰሩም ድልድይ ባለመገንባቱ ምክንያት መንገዶቹ በጎርፍ ለጉዳት እየተጋለጡ ለህብረተሰቡ ተገቢውን አገልግሎት እየሰጡ እንዳልሆነ ተናግረዋል።

የማረቆ ልዩ ወረዳ አስተዳዳሪ አቶ ንጉሴ መኬ በበኩላቸው የቆሼ ጦራ-ሚቶ መንገድ ግንባታ ከካሳ ክፍያ ጋር በተያያዘ መስተጓጎሉን ጠቅሰው፣ የመንገድ ጥገናም መዘግየት በአካባቢው ማህበረሰብ የእለት ተእለት እንቅስቃሴ ላይ ጫና መሳደሩን ገልጸዋል።

በልዩ ወረዳው በሚገኙ ሁለት ቀበሌዎች በቂ የንፁህ መጠጥ ውሃ አቅርቦት ባለመኖሩ ህብረተሰቡ ለችግር መዳረጉንም አንስተዋል።

የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ እንዳሻው ጣሰው በክልሉ ለረዥም ዘመናት ግንባታቸው ተጀምሮ ያልተጠናቀቁ የተለያዩ ፕሮጀክቶች መኖራቸውን አንስተዋል።

የክልሉ መንግስት ፕሮጀክቶቹ ያለባቸውን ችግር ለማቃለል በቀጣይ ትኩረት ሰጥቶ እንደሚሰራ አረጋግጠዋል።

በመንግስት ሊከፈል የሚገባ የካሳ ክፍያ በፍጥነት የሚፈጸምበትን ሁኔታ በማመቻቸት ግንባታቸው የዘገዩ የልማት ፕሮጀክቶች በአጭር ጊዜ ውስጥ እንዲጠናቀቁ ለማድረግ እንደሚሰራም አስታውቀዋል።

በየአካቢቢው የልማት ፕሮጀክቶች ያለምንም ችግር እንዲከናወኑና ፕሮጀክቶቹ ለታለመላቸው ዓላማ እንዲውሉ በየደረጃው ያለው አመራር በቁርጠኝነት ሊሰራ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

የመንገድና የውሃ መሰረተ ልማት ፕሮጀክቶች ግንባታ ሂደት ስኬታማ እንዲሆን አስፈላጊውን ክትትልና ቁጥጥር ማድረግ እንደሚገባም አሳስበዋል።

ለአንድ ቀን በተዘጋጀው የውይይት መድረክ ላይ  በየደረጃው ያሉ አመራሮችና ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም