ቀጥታ፡

ኤስዋቲኒ ከኢትዮጵያ ጋር በአቪዬሽን መስክ በጋራ ለመሥራት ፍላጎት አላት - የአገሪቷ ጠቅላይ ሚኒስትር ሩሴል ድላሚኒ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 12/2016(ኢዜአ)፦ ኤስዋቲኒ ከኢትዮጵያ ጋር በአቪዬሽን መስክ በጋራ ለመሥራት ፍላጎት እንዳላት የአገሪቷ ጠቅላይ ሚኒስትር ሩሴል ድላሚኒ ገለጹ። 

የአገሪቷ ጠቅላይ ሚኒስትር ሩሴል ድላሚኒ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ አገራቸው ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን የሁለትዮሽ ግንኙነት ወደ ላቀ ደረጃ ለማሳደግ ፍላጎት አላት።

በተለይም በአሁኑ ወቅት በአፍሪካ ስመ-ጥርና ግዙፉ ከሆነው የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ በአቪዬሽን ሴክተር በጋራ ለመሥራት እንቅስቃሴ መጀመራቸውን ገልፀዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በ37ኛው አፍሪካ ኅብረት ጉባዔ ለመሳተፍ ኢትዮጵያ በነበሩበት ወቅት አየር መንገዱን የመጎብኘትና ከአየር መንገዱ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ጋር የመነጋገር ዕድል ማግኘታቸውንም ነው ያነሱት።

ኤስዋቲኒ ከኢትዮጵያ አየር መንገድ ጋር በጋራ ብትሰራ ውጤታማ እንደምትሆን ገልጸው፤ ይህንኑ ከግምት በማስገባት በዘርፉ ውጤታማ አጋርነት ለመፍጠር ትኩረት መደረጉንም ተናግረዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ኢትዮጵያ ቅኝ ያልተገዛች አገር መሆኗን አንስተው፤ በዚህም ኢትዮጵያ የሁሉም የአፍሪካውያን ኩራት መሆኗን አንስተዋል።

በሌላ በኩል አህጉሪቷን ወደ ብልጽግና ለማቅናት አፍሪካውያን በጋራ መቆምና ለሚያጋጥሙ ችግሮች አህጉራዊ መፍትሔ ማፈላለግ ወሳኝ መሆኑን ገልፀዋል።

የአፍሪካን አህጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጣና ውጤታማ እንዲሆን አገራቱ በመሠረተ-ልማት፣ በአየር ትራንስፖርትና መሰል ተግባራት ትስስር መፍጠር ይገባል ብለዋል።

ይህንንም እውን ለማድረግ አገራት በጋራ መሥራት ይጠበቅባቸዋል ነው ያሉት።

አፍሪካ የበርካታ የተፈጥሮ ፀጋና ከፍተኛ ቁጥር ያለው ወጣት ባለቤት መሆኗን ጠቅሰው፤ እነዚህን ፀጋዎች በመጠቀም ወደ ተጨባጭ ኃብት መለወጥ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም