ቀጥታ፡

አዲሱ የአምራች ኢንዱስትሪ ፖሊሲ ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነትን ለማሳደግ ጉልህ ድርሻ አለው -- የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር

ሀዋሳ፤የካቲት 12/2016 (ኢዜአ)፡-አዲሱ የአምራች ኢንዱስትሪ ፖሊሲ ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነትን በማሳደግ ለሀገር በቀል ኢኮኖሚ ሪፎርሙ ተፈጻሚነት ጉልህ ድርሻ እንዳለው የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ገለጸ።

ሚኒስቴሩ ከሲዳማ ክልል ጋር በተመባበር ለክልሉ አመራሮችና ባለድርሻ አካላት በአዲሱ የአምራች ኢንዱስትሪ ፖሊሲ ላይ የግንዛቤ መፍጠሪያ መድረክ በሀዋሳ አካሂዷል።


 

ሚኒስትሩ አቶ መላኩ አለበል በዚህ ጊዜ እንደገለጹት ላለፉት 21 ዓመታት በሀገሪቱ ሲተገበር የነበረው የኢንዱስትሪ ፖሊሲ አሁን ያለውን የዓለም ነባራዊ ሁኔታ ያላገናዘበ በመሆኑ መቀየር አስፈላጊ ሆኗል።

ይህንን ተከትሎ በመንግሥት የተዘጋጀው አዲሱ የአምራች ኢንዱስትሪ ፖሊሲ አለምአቀፍ ተወዳዳሪነትን በማሳደግ ለሀገር በቀል ኢኮኖሚ ሪፎርሙ ተፈጻሚነት ጉልህ ድርሻ እንዳለው አመላክተዋል።

በርካታ ውስንነቶች ያሉበትን የኢንዱስትሪ ዘርፍ ውጤታማነት ለማረጋገጥ ዘመኑን የዋጀ ፖሊሲ ማስፈለጉን ገልጸው ላለፉት ሶስት ዓመታት ዓለም አቀፍ አማካሪዎችን ያሳተፈ ጥናት መደረጉንም ጠቅሰዋል።

የምርት ልማትና ተወዳዳሪነት፣ የሰው ሃይል አጠቃቀም፣ ቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን፣ የማክሮ ኢኮኖሚ ስነ-ምህዳርና ፋይናንስ ጨምሮ የተበታተኑ ኢንዱስትሪዎችን በአንድ ማእከል ማሰባሰብ በፖሊሲው ትኩረት ከተደረገባቸው ጉዳዮች መካከል ተጠቃሽ መሆናቸውንም ገልጸዋል።

ኢንዱስትሪዎች የጠንካራ ፖሊሲና አስፈጻሚዎች ውጤት ናቸው ያሉት ሚኒስትሩ በየደረጃው ያሉ አመራሮችና ባለድርሻ አካላት በፖሊሲው ላይ ተገቢውን ግንዛቤ ይዘው ለተፈጻሚነቱ አበክረው እንዲሰሩ አሳስበዋል።

በተለይ የሲዳማ ክልል በኢንዱስትሪ ዘርፍ ተወዳዳሪ ለመሆን የሚችል አቅም ያለው በመሆኑ አመራሩ በትኩረት ሊሰራበት እንደሚገባ ገልጸዋል።

የሲዳማ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ደስታ ሌዳሞ በበኩላቸው በክልሉ ለኢንዱስትሪው ዘርፍ የሚደረገው ትኩረት ከፍተኛ መሆኑን ገልጸዋል።


 

በዚህም ከሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር በክልሉ ያለውን የኢንዱስትሪ አቅም የሚያሳይ የመሬት ካርታ መዘጋጀቱን ተናግረዋል።

ፈጣን የኢንዱስትሪ ለውጥ ለማረጋገጥም የኢንዱስትሪ ዞን ማቋቋምና አስፈላጊውን መሰረተ ልማት የማሟላት ስራ በትኩረት እየተከናወነ ነው ብለዋል።

አዲሱ የአምራች ኢንዱስትሪ ፖሊሲም በክልሉ የተጀመረውን እንቅስቃሴ እንደሚያግዝ ገልጸው አመራሩ ተገቢውን ግንዛቤ በመጨበጥ ከፖሊሲው የሚመነጩ ተልእኮዎችን ለማስፈጸም መስራት እንዳለበት ገልጸዋል።

የአምራች ኢንዱስትሪው ዘርፍ በርካታ ባለድርሻ አካላትን የሚያሳትፍ መሆኑን የገለጹት ደግሞ የሲዳማ ክልል ኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ ሃላፊ አቶ ጎሳዬ ጎዳና ናቸው።


 

ለበርካታ ዓመታት ስራ ላይ የነበረው ፖሊሲ ያሉበትን በርካታ ውስንነቶች የሚፈታው አዲሱ የአምራች ኢንዱስትሪው ፖሊሲ ዘርፉን ለማነቃቃት ከፍተኛ ድርሻ ያለው መሆኑን ገልጸዋል።

ክልሉ ያለውን የኢንዱስትሪ አቅም በፖሊሲ በማገዝ ለኢኮኖሚያዊ ለውጥ እንደሚሰራ ነው የቢሮው ኃላፊ ያስታወቁት።

በመድረኩ አዲሱ የአምራች ኢንዱስትሪ ፖሊሲ በያዛቸው ዝርዝር ጉዳዮችና አተገባበሩ ላይ ያተኮረ ሰነድ ቀርቦ ሰፊ ውይይት የተደረገበት ሲሆን በየደረጃው ያሉ የክልሉ ከፍተኛ አመራሮችና ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል።

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም