ኢትዮ ቴሌኮም ዲጂታል ኢትዮጵያን እውን በማድረግ ሂደት ውስጥ የመሪነቱን ሚና እየተወጣ ይገኛል

358

አዲስ አበባ፤ የካቲት 12/2016(ኢዜአ)፦ኢትዮ ቴሌኮም ዲጂታል ኢትዮጵያን እውን በማድረግ ሂደት ውስጥ የመሪነቱን ሚና እየተወጣ እንደሚገኝ የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ስራ አስፈጻሚ ፍሬህይወት ታምሩ ገለጹ።

ኢትዮ ቴሌኮም በኢትዮጵያ ሁለንተናዊ የዕድገት ግስጋሴ ውስጥ ከፍተኛ ሚና ከሚጫወቱ የመንግስት የልማት ድርጅቶች ውስጥ በግንባር ቀደምትነት ይጠቀሳል።

ኩባንያው ከመደበኛ አገልግሎቱ ባሻገር የፋይናንስ አካታችነትን በማረጋገጥ እና የዲጂታል አገልግሎቶችን በስፋት ተደራሽ በማድረግ የዲጂታል ኢትዮጵያን ራዕይ ለማሳካት በርካታ ሥራዎችን በማከናወን ላይ ይገኛል።

ይህን ተከትሎ ኩባንያው ባለፉት የለውጥ ዓመታት የኢንተርኔት ተጠቃሚ ደንበኞቹን ቁጥር በ 104 በመቶ ማሳደግ መቻሉ ተገልጿል።

ከ ኢዜአ ጋር ቆይታ ያደረጉት የኩባንያው ዋና ስራ አስፈጻሚ ፍሬህይወት ታምሩ እንዳሉት ኩባንያው ዜጎች ቴክኖሎጂን ተጠቅመው የእለት ተእለት እንቅስቃሴያቸውን እንዲያቀላጥፉ የሚረዱ ምቹ ሁኔታዎችን እየፈጠረ ይገኛል።

እንዲሁም ተቋማት ውጤታማ እንዲሆኑ፣ አገልግሎታቸውን በፍጥነት ተደራሽ እንዲያደርጉና ምርታማነታቸው እንዲጨምር የሚረዱ ቴክኖሎጂዎችን ተደራሽ ማድረግ መቻሉን ተናግረዋል፡፡

ከዚህ ባለፈ ቴክኖሎጂን መሰረት ያደረጉ አዳዲስ የስራ እድሎችን ለመፍጠር የሚያስችሉ በርካታ ትሩፋቶችን ማበርከቱን ተናግረዋል።

ከለውጡ በፊት የነበሩት የኩባንያው ደንበኞች 37 ሚሊዮን እንደነበሩ በማስታወስ በ 2016 አጋማሽ ይህ ቁጥር 74 ነጥብ 6 ሚሊዮን መድረሱን ጠቁመዋል።

ውጤቱ የተገኘው ሪፎርሙን ተከትሎ በተከናወኑ ስራዎች እና በየጊዜው በሚደረጉ ማሻሻያዎች መሆኑን ገልጸው ምጣኔው የ97 በመቶ ዕድገት የታየበት መሆኑን አንስተዋል።

ከዚህ ቀደም የነበረው የኢንተርኔት ተጠቃሚዎች ቁጥር 17 ነጥብ 8 ሚሊዮን እንደነበር ገልጸው አሁን ላይ ይህ ቁጥር 36 ነጥብ 4 ሚሊዮን መድረሱን ተናግረዋል።

መንግስት ለዜጎች የሚሰጠውን አጠቃላይ አገልግሎት ዲጂታላይዝ ለማድረግ በሚደረገው ጥረት ውስጥ ኢትዮ ቴሌኮም አስቻይ ሁኔታዎችን የመፍጠር ስራዎቹን በጥራት እየተወጣ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

ቀደም ሲል 20 በመቶ የነበረው የስማርት ስልክ ተደራሽነት አሁን ላይ ወደ 46 በመቶ ማደጉን ጠቁመዋል።

ለዕድገቱ መሰረት የሆነውን ቴክኖሎጂ በማዳረስ ረገድ አሁን ላይ 340 የሚሆኑ ከተሞች የ 4ጂ አገልግሎት እንዲያገኙ መደረጉን ተናግረዋል።

የብሮድባንድ አገልግሎት ከአንድ ሀገር ዕድገት ጋር ቀጥታ ግንኙነት እንዳለው ገልጸው አሁን ላይ የተጠቃሚ ደንበኞች ቁጥር  688 ሺህ መድረሱን ገልጸዋል።

በዚህም በርካታ ተቋማት ያለምንም የቴክኖሎጂ ውስንነት በሀገር ውስጥ እና በውጭ ስራቸውን መከወን የሚችሉበት ምቹ ሁኔታ መፈጠሩን ተናግረዋል።

ኩባንያው ዲጂታል ኢትዮጵያን እውን በማድረግ ሂደት ውስጥ የመሪነቱን ሚና እየተወጣ እንደሚገኝ ዋና ስራ አስፈጻሚዋ አስታውቀዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም