ቀጥታ፡

በአፍሪካ ዘላቂ ልማትና ሰላምን ለማረጋገጥ አገራት በትምህርት ዘርፍ መሥራት አለባቸው - ዶክተር ንኮሳዛና ድላሚኒ ዙማ 

አዲስ አበባ፤ የካቲት 12/2016(ኢዜአ)፦በአፍሪካ ዘላቂ ልማትና ሰላምን ለማረጋገጥ ሀገራት በትምህርት ዘርፍ በትኩረት መሥራት እንደሚገባቸው የቀድሞ የአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን ሊቀ-መንበር ዶክተር ንኮሳዛና ድላሚኒ ዙማ ተናገሩ።

የመንግሥታቱ ድርጅት መረጃ እንደሚያሳየው፤ በአፍሪካ በተለይም ከሰሃራ በታች በሚገኘው የአህጉሪቱ ቀጣና በዓለም የትምህርት ተደራሽነት ካልተረጋገጠበት አካባቢ ቀዳሚ ነው። 

ለአብነትም አጠቃላይ በአህጉሪቱ ከሚገኙ እድሜያቸው ከ15 እስከ 17 የሚሆኑ ታዳጊ ወጣቶች 60 በመቶ የሚሆኑት ከትምህርት ገበታ ውጪ ናቸው፤ ትምህርታቸውን የሚያቋርጡ ታዳጊዎች ቁጥርም ከፍተኛ ነው። 

በቂ መምህራን የማሰማራት እንዲሁም አህጉሪቱን ለመለወጥ የሚያስችሉ በዘመናዊ ቴክኖሎጂ የተደገፉ የተግባር ተኮር  ትምህርቶችን ተደራሽነትም ከሚፈለገው በታች ነው።

ይህንን ከግምት በማስገባት በተጠናቀቀው 37ኛው የአፍሪካ ኅብረት የመሪዎች ጉባኤ የዘንድሮውን የፈረንጆች ዓመት የትምህርት ዘመን አድርጎ በዘርፉ ትኩረት እንዲደረግ አቅጣጫ አስቀምጧል።

በጉባኤው የተሳተፉት ዶክተር ንኮሳዛና ድላሚኒ ዙማ ለኢዜአ እንደተናገሩት በአፍሪካ ዘላቂ ልማትና ሰላም የማረጋገጥ ጉዳይ አሁንም ትኩረት ሊደረግበት የሚገባ ዐቢይ ጉዳይ መሆኑን አንስተዋል። 

የአፍሪካ አገራት በተለይም ሰላምን ለማረጋገጥ በተለይም ወጣቶች በግጭት እንዳይሳተፉ ለማድረግ የሚያስችላቸውን የሥራ እድል ፈጠራ ማስፋት እንደሚገባቸው ተናግረዋል። 

እንደ እርሳቸው ገለጻ፤ ወጣቶች የሥራ እድል ተጠቃሚ ከሆኑ በግጭት አይሳተፉም።

ወጣቶች የሥራ እድል ፈጣሪና ተጠቃሚ እንዲሆኑ በተለያዩ የሙያ መስክ መሰልጠን እንዳለባቸው ገልጸው፤ ለዚህም የወጣቶች ትምህርትና ሥልጠና ቁልፍ ጉዳይ መሆኑን ነው የገለጹት።   

በተጓዳኝም፤ አህጉሪቷ በርካታ የተፈጥሮ ጸጋዎች ባለቤት መሆኗን ገልጸው፤ እነዚህን ጸጋዎች ወደ ተጨባጭ ኃብት ለመቀየር የሰለጠነ የሰው ኃይል ማፍራት ይገባል ብለዋል።    

ለዚህም ትምህርት ወሳኝ መሆኑን ጠቅሰው አገራት በአህጉሪቱ በርካታ አዎንታዊ ለውጦች ለማስመዝገብ በትምህርት ዘርፍ ትኩረት አድርገው ሊሰሩ እንደሚገባ መክረዋል። 

ይህንን ተከትሎ የአፍሪካ አገራት በተለይም የትምህርት የሙያና የሥልጠና ዘርፉን ጨምሮ' ተደራሽነትና ጥራት አበክረው ሊሰሩ እንደሚገባ አመላክተዋል።  

አህጉሪቱ ያላትን ጸጋዎች ጥቅም ላይ ለማዋል የሚያስችል የመማር ማስተማር ሥልት ገቢራዊ እንዲደረግ ጠይቀው፤ በተለይም ዘመናዊ ቴክኖሎጂን የዋጀ የትምህርት ሥርዓት አስፈላጊ መሆኑንም ጠቁመዋል።    

ለዚህም በትምህርት ዘርፍ ያለውን ኢንቨስትመንት መጨመር እንደሚገባ ምክረ ኃሳብ ሰጥተዋል። 

በሌላ በኩል የአፍሪካ አገራት ዘላቂ ልማትን ለማረጋገጥ እንቅፋት የሆነውን የጸጥታ መደፍረስ እልባት ለመስጠት ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በቅርበት መሥራት ይገባቸዋል ብለዋል። 

የአፍሪካ ድምጽ በዓለም አቀፍ መድረኮች ተሰሚነቱን ለመጨመርና የአህጉሪቱ ፍላጎትን ያማከለ የባለብዙ ወገን ተቋማት ለመገንባት የተጀመሩ ጥረቶች ተጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸው ገልጸዋል። 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም