ከተሜው ገበሬ - ኮማንደር ጥላሁን ጸጋዬ - ኢዜአ አማርኛ
ከተሜው ገበሬ - ኮማንደር ጥላሁን ጸጋዬ
የከተማ ግብርና ሥራ ኢኮኖሚን ከመደገፍ ባለፈ ጤናማ ማህበረሰብ እንዲፈጠር አበርክቶው የጎላ ነው።
አዲስ አበባ በመኖሪያ እና በተቋማት ቅጥር ግቢዎች የጓሮ አትክልት፣ ፍራፍሬና መሰል የግብርና ልማት ስራዎች እየተስፋፉባቸው ከመጡ ከተሞች መካከል አንዷ ናት።
በርካታ የመዲናዋ ነዋሪዎች በግቢያቸው በሚያለሟቸው አትክልትና ፍራፍሬዎች ራሳቸውን ከመመገብ ባለፈ ለሌሎች መትረፍ ችለዋል።
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እህት ኩባንያ የሆነው ኮሜርሻል ኖሚኒስ ዳይሬክተር ጄኔራል የሆኑት ኮማንደር ጥላሁን ጸጋዬ በከተማ ግብርና አርአያ የሆነ ስራ እያከናወኑ ይገኛሉ።
በአዲስ አበባ ከተማ አቃቂ ቃሊቲ አካባቢ ተወልደው ያደጉት ኮማንደር ጥላሁን የጓሮ አትክልትና ፍራፍሬ በማምረት ተጠቃሚ ከመሆን ባለፈ የገቢ ምንጭም ሆኗቸዋል።
የከተማ ግብርና ስራን ከቤተሰቦቻቸው መውረሳቸውን ያስታወሱት ኮማንደር ጥላሁን የከተማ ግብርና የኑሮ ውድነትን ለመቋቋም ከማገዙ ባለፈ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ እድል እንደሚፈጥር ይገልጻሉ።
ከመደበኛ ሥራቸው ጎን ለጎን እንደ ጥቅል ጎመን፣ ቆስጣ፣ ሰላጣ፣ አፕል፣ ሙዝ፣ ቡና፣ ማር፤ ዘይቱን እና ሌሎች ተክሎችን በጓሯቸው በማምረት ለቤተሰቦቻቸው ፍጆታ እየተጠቀሙ ይገኛሉ።
ከዚህም ባለፈ ቡና፣ ሸንኮራ፣ ማር በማምረት ከራስ ፍጆታ አልፎ ለሌሎችም መትረፍ መቻላቸውን ይናገራሉ።
በተለይም በከተማ ግብርና ለመሰማራት ወሳኙ ሰፊ ወይም ጠባብ ቦታ መኖር ሳይሆን ያለውን ሃብት በአግባቡ በመጠቀም በፍላጎት መስራት መሆኑን ያነሳሉ።
በዶሮ እርባታም በስፋት ለመሰማራት እየሰሩ ሲሆን በዚህም ከራሳቸው ፍጆታ አልፈው ቢያንስ ለአካባቢው ማህበረሰብ በተመጣጣኝ ዋጋ እንቁላል ለማቅረብ ተዘጋጅተዋል።
አሁን ላይ በመንግስት እየተተገበረ ያለው የከተማ ግብርና ከድህነት ለማምለጥ ሁነኛ መፍትሄ መሆኑን ገልጸዋል።
በቀጣይም በተለይም ስራውን ይበልጥ በማስፋት ከራሳቸው አልፈው ምርቶቻቸውን ለማህበረሰቡ በተመጣጣኝ ዋጋ ለማቅረብ እየሰሩ እንደሆነ ተናግረዋል።
ማንም ሰው ምንም አይነት ስራ ለመስራት በመጀመሪያ ደረጃ ፍላጎት ሊኖረው እንደሚገባ የገለጹት ኮማንደር ጥላሁን፤ በፍላጎት ወደ ስራ ከተገባ ውጤታማ መሆን እንደሚቻል ተናግረዋል።
ሁሉም የቤተሰቡ አባላት አትክልትና ፍራፍሬዎችን በመንከባከብ የሚያደርጉት አስተዋጽኦ ለውጤታማነታቸው መሰረት መሆኑን ገልጸው አንድን ነገር ለማሳካት በቤተሰብ ውስጥ የሀሳብ መግባባትና መተባበር ወሳኝ መሆኑንም ገልጸዋል።