ቀጥታ፡

በተለያዩ የትብብር መስኮች ላይ የተመሠረተውን የኬንያና የኢትዮጵያ ግንኙነት ለማጠናከር ይሰራል 

አዲስ አበባ፤ የካቲት 12/2016(ኢዜአ)፦ኢትዮጵያና ኬንያ በተለያዩ የትብብር መስኮች ላይ የተመሠረተው አጋርነታቸውን ለማጠናከር እንደሚሰሩ ገለጹ።

36ኛው የኢትዮ-ኬንያ የጋራ የሚኒስትሮች ኮሚሽን ስብሰባ በአዲስ አበባ እየተካሄደ ነው።


 

ስብሰባው ሁለቱ አገራት እስካሁን የተፈራረሙትን የሁለትዮሽ ሥምምነት አፈጻጸም ለመገምገምና የአገራቱን ግንኙነት ለማጠናከር በሚቻልባቸው ጉዳዮች ለመምከር ያለመ ነው።

በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የአፍሪካ ጉዳዮች ዳይሬክተር ጄኔራል አምባሳደር ፍስሃ ሻወል በዚሁ ጊዜ እንደገለጹት፤ ኢትዮጵያና ኬንያ ጠንካራ ወዳጅነት ያላቸው አገራት ናቸው። 

አገራቱ በመልክዓ-ምድር፣ በባህል፣ በቋንቋና በሌሎች ጉዳዮች የተሳሰሩ መሆናቸውን ጠቁመው፤ በሰላምና ደኅንነት እንዲሁም በልማት መስክ በትብብር እየሰሩ መሆኑንም ገልፀዋል።   

ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ የመጣውን የሁለቱን አገራት ወንድማማችነት ይበልጥ ለማጠናከር ኢትዮጵያ ቁርጠኛ መሆኗን ገልጸው፤ ይህን ለማስቀጠል እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

ሁለቱ አገራት በቀጣናዊ ጉዳዮች ያላቸውን ትብብር ለማጠናከር እየተሰራ መሆኑንም እንዲሁ። 

በአዲስ አበባ እየተካሄደ ያለው የኢትዮ-ኬንያ የጋራ ሚኒስትሮች ኮሚሽን ስብሰባው በተለያዩ መስኮች የተመሠረተውን የሁለቱ አገራት ግንኙነት ለማጠናከር ፋይዳው የጎላ መሆኑን ጠቁመዋል።  

የኬንያ የውጭ ጉዳይ አገልግሎት፣ ፖለቲካዊና ዲፕሎማሲያዊ ጉዳዮች ዳይሬክተር ጄኔራል አምባሳደር ሞይ ሌሞሺራ በበኩላቸው፤ ኬንያና ኢትዮጵያ ታሪካዊ ግንኙነት ያላቸው አገራት ናቸው ብለዋል።

አሁን ላይ በቀጣናውና በዓለም አቀፍ ደረጃ ያሉት ለውጦች ሁለቱ አገራት በሁለትዮሽ፣ በቀጣናዊ፣ በአህጉራዊና በዓለም አቀፍ ጉዳዮች ያላቸውን ግንኙነት ለማጠናከር ያስፈልጋቸዋል ብለዋል።

ኬንያ ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ግንኙነት ለማጠናከር ቁርጠኛ መሆኗን ተናግረው፤ በሚቀጥሉት ዓመታት ለጋራ ብልጽግና ታሪካዊ ግንኙነቱን ለማጠናከር እንደሚሰራ አምባሳደሩ አረጋግጠዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም