ኢትዮጵያ በአፍሪካ በምግብ ራስን ለመቻል የተቀመጠውን የግብርና ዘርፍ 6 በመቶ ዓመታዊ እድገት በተከታታይ እያሳካች ነው - ግርማ አመንቴ (ዶ/ር) - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ በአፍሪካ በምግብ ራስን ለመቻል የተቀመጠውን የግብርና ዘርፍ 6 በመቶ ዓመታዊ እድገት በተከታታይ እያሳካች ነው - ግርማ አመንቴ (ዶ/ር)
አዲስ አበባ፤ የካቲት 12/2016 (ኢዜአ)፦ኢትዮጵያ አፍሪካውያን በምግብ ራሳቸውን እንዲችሉ የተቀመጠውን የ6 በመቶ የግብርና ዘርፍ ዓመታዊ እድገት በተከታታይ እያሳካች መሆኗን የግብርና ሚኒስትር ዶክተር ግርማ አመንቴ ገለጹ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በአፍሪካ ኅብረት የአፍሪካ አጠቃላይ የግብርና ልማት ፕሮግራም መሪነታቸው የፕሮግራሙን አራተኛ የግምገማ ሪፖርት ለኅብረቱ አባል አገራት መሪዎች አቅርበዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ የኢትዮጵያን የግብርና ዘርፍ ዕድገት በሪፖርታቸው አካተው አብራርተዋል።
የአፍሪካ አጠቃላይ የግብርና ልማት ፕሮግራም (CAADP) ለአፍሪካ የግብርና ትራንስፎርሜሽን፣ ኃብት ፈጠራ፣ የምግብ ዋስትናና የተመጣጠነ ምግብ አቅርቦት፣ የምጣኔ ኃብት እድገትና ብልጽግና የፖሊሲ ማዕቀፍ ሆኖ የሚያገለግል ነው።
በአህጉሪቱ የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ በተዘጋጀው በዚህ አህጉራዊ ፕሮግራም መሰረት አገራት ከዓመታዊ በጀታቸው 10 በመቶውን ለግብርና ለማዋል ተስማምተዋል።
አፍሪካዊ ግብን ለማሳካትም እያንዳንዱ አገር በዓመት ስድስት በመቶ የግብርና ዘርፍ እድገት ለማስመዝገብ እንዲሰሩ አቅጣጫ ተቀምጧል።
የግብርና ሚኒስትሩ ዶክተር ግርማ አመንቴ እንደገለጹት፥ አፍሪካ ሰፊ ለም አፈርና ውሃ ቢኖራትም አብዛኛው የእርሻ ሥራዋ ኋላቀርና በቂ ምርት የማይገኝበት የአመራረት ዘይቤን የሚከተል ነው።
ከኢትዮጵያም ለበርካታ ዓመታት በዚሁ መንገድ መቀጠሏን አውስተው፥ ከአገራዊ ለውጡ ወዲህ ግን በግብርናው ዘርፍ ላይ ስር ነቀል ለውጥ እያካሄደች ነው ብለዋል።
ለኩታገጠም እርሻ፣ ለበጋ መስኖ ልማት፣ ለአትክልትና ፍራፍሬ፣ ለሌማት ትሩፋትና በአረንጓዴ አሻራ ለአካባቢ ጥበቃ ሰፊ ትኩረት ሰጥታለች ብለዋል።
የአፍሪካ አጠቃላይ የግብርና ልማት ፕሮግራም መሪ እንደመሆኗ ግብርናውን በማዘመን ባለፉት 3 ዓመታት የስድስት በመቶ እድገት በማስመዝገብ አህጉራዊ ግቧን እያሳካች ነው ብለዋል።
በአህጉር ደረጃ የግብርና ዘርፉን ለማዘመን የተቀመጠው አንድኛው አቅጣጫ በቂ የፋይናነስ አቅርቦትና ኢንቨስትመንትን ማስፋፋት ቢሆንም በታሰበው ልክ ፈሰስ እየተደረገለት አይደለም ይላሉ።
ለዚህም ምክንያቱ ብዙዎቹ የፋይናንስ ተቋማት የግብርናውን መስክ አክሳሪ ዘርፍ እድርገው ስለሚወስዱት መሆኑን ጠቅሰዋል።
የኢትዮጵያ መንግስት ባለፉት ዓመታት የፖሊሲ ለውጥ በማድረግ ለዘርፉ የተሻለ ፋይናንስ ለማቅረብ ጥረት ማድረጉን ገልጸዋል።
በአስተሳሰብ ደረጃም ግብርና የድህነት መገለጫ ሳይሆን የኃብት መፍጠሪያ መንገድ መሆኑን የዕይታ ለውጥ እየተፈጠረ ነው ይላሉ።
በዘርፉ የተመዘገቡ ተጨባጭ ለውጦችም አህጉራዊና ዓለም አቀፋዊ ተቋማት የፋይናንስ ድጋፍ ለማድረግ ፍላጎት እንዲያሳዩና በተግባርም አንድ እርምጃ እንዲራመዱ ማድረጉን ገልጸዋል።
የአህጉሪቱን የምግብ ዋስትና ለማረጋገጥ ፈታኝ ከሆኑ ጉዳዮች አንዱ በዝናብ ጥገኝነት ላይ ከተመሰረተ ግብርና አለመላቀቃችን ነው ብለዋል።
ይህም የአየር ንብረት ለውጥ በሚፈጥራቸው አደጋዎች ዘርፉ በተከታታይ ጉዳት እንዲያስተናግድ ማድረጉን መሆኑንም በመጠቆም።
ኢትዮጵያም ለረጅም ዓመታት በዝናብ ወቅት የተመሰረተ እርሻን እየተከተለች መሆኗን አውስተው፥ ይህን ለመቀየር የበጋ መስኖ ልማት ኢኒሼቲቭ መጀመሩን ገልጸዋል።
በዚህም በበጋ መስኖ ስንዴ ልማት ከ3 ሺህ ሄክታር በመነሳት በአሁኑ ወቅት 3 ሚሊዮን ሄክታር እየለማ ሲሆን ከዚህም 120 ሚሊዮን ኩንታል ምርት እንደሚገኝ አመላክተዋል።
እንደ ሀገር በመስኖ ሊለማ ከሚችለው 10 ሚሊዮን ሄከታር ውስጥ በቂ መሰረተ ልማት ያለው ግን 1 ነጥብ 5 ሚሊዮን ሄክታር ብቻ ነው ያሉት ሚኒስትር፥ ይህን ለማስፋት አውታሮች እየተገነቡ መሆኑን አንስተዋል።
ከዚህም ባለፈ አነስትኛ ይዞታ ላላቸው አርሶ አደሮች ትናንሽ የውሃ መሳቢያን በማደል መስኖ ልማትን ለማስፋፋት በትኩረት እንደሚሰራ ነው የገለጹት።
ኢትዮጵያ በምግብ ራስን ለመቻል የተያዘውን አህጉራዊ ግብ በማሳካት ተምሳሌትነቷን እንደምታረጋግጥም ገልጸዋል።
ግብርናውን ለማዘመን ከ500 በላይ ለዘርፉ ጥቅም የሚሰሩ መሳሪያዎች ከቀረጥ ነጻ እንዲገቡ መወሰኑን አስታውሰዋል።