እያደገ የመጣውን የሀገሪቱ ኢኮኖሚ የሚፈልገውን የኤሌትሪክ አገልግሎት ለማሟላት እየተሰራ ነው- የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት - ኢዜአ አማርኛ
እያደገ የመጣውን የሀገሪቱ ኢኮኖሚ የሚፈልገውን የኤሌትሪክ አገልግሎት ለማሟላት እየተሰራ ነው- የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት
አዲስ አበባ፤ የካቲት 12/2016(ኢዜአ)፦ እያደገ የመጣውን የሀገሪቱ ኢኮኖሚ የሚሸከም የኤሌክትሪክ አገልግሎት ለመስጠት በቁርጠኝነት እየተሰራ መሆኑን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ገለፀ።
አገልግሎቱ በተያዘው በጀት ዓመት ባለፉት ስድስት ወራት 19 ቢሊየን ብር የሚጠጋ ገንዘብ መሰብሰቡንም አስታውቋል።
የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ዋና ሥራ አስፈጻሚ ሽፈራው ተሊላ ከኢዜአ ጋር ቆይታ አድርገዋል።
ተቋሙ በኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግ ሥር ከተቋቋመ አንስቶ አስተማማኝ እና ዘመኑን የሚመጥን የኤሌክትሪክ አገልግሎት ለመስጠት የትኩረት መስኮችን ለይቶ እየሰራ መሆኑንም ገልፀዋል።
ከዚሁ ውስጥም የመሠረተ-ልማቱን የአቅም ውስንነት የማሻሻል ሥራ በማከናወን ከኢኮኖሚው እድገት ጋር ተያይዞ እየታየ ያለውን ፍላጎት የማሟላት ሥራ አንዱ ነው ብለዋል።
በተለይም በከተሞች በኢንዱስትሪው መስክ የሚቀርበውን የአዳዲስ ደንበኞችን ፍላጎት የማስተናገድ ሥራም እንዲሁ ከተለዩት የትኩረት መስኮች መካከል ተጠቃሽ እንደሆኑ ጠቁመዋል።
ለዚህም ውጤታማነት የመሠረተ-ልማቱን አቅም የማሳደግና የማስፋፋት ሥራም እየተሰራ መሆኑንም አቶ ሽፈራው ተናግረዋል።
የተጀመረው የመሠረተ-ልማቱን የማሳደግ ሥራ የሀገሪቱ ኢኮኖሚን መመገብ እንዲችልም እየተሰራ መሆኑንም ዋና ሥራ አስፈጻሚው ተናግረዋል።
ተቋሙን በሰው ኃይል የመገንባትና ደንበኛው ወቅቱን ያማከለ ዘመናዊ አገልግሎት እንዲያገኝ የማድረግ ሥራም እንዲሁ።
ይህም ተቋሙን ተወዳዳሪ ለማድረግና ለተለያዩ ኢንቨስትመንቶች ምቹ ሁኔታዎችን ለመፍጠር እንደሚረዳም ነው የገለጹት።
እንደ አቶ ሽፈራው ገለፃ፤ ተቋሙ ካስቀመጣቸው ዕቅዶቹ ውስጥ አዳዲስ ደንበኞችን የማግኘት ሥራ መሆኑንም ገልፀዋል።
በዚህ መሠረትም ባለፉት ስድስት ወራት 200ሺህ የሚጠጉ ደንበኞች አገልግሎት እንዲያገኙ የተደረገ ሲሆን፤ 19 ቢሊየን ብር ገቢ ለማግኘት መቻሉንም አስረድተዋል።
በዚሁ ስድስት ወር ውስጥ በገጠር ከተሞችም 35 ለሚሆኑ አካባቢዎች የኃይል ተጠቃሚ ለማድረግ መቻሉንም አስረድተዋል።