የአሁኑ ትውልድ የአባቶቹን አኩሪ ገድል ከመዘከር ጎን ለጎን የራሱን ታሪክ ሰርቶ ለማለፍ በቁርጠኝነት እየሠራ ይገኛል -ከንቲባ አዳነች አቤቤ - ኢዜአ አማርኛ
የአሁኑ ትውልድ የአባቶቹን አኩሪ ገድል ከመዘከር ጎን ለጎን የራሱን ታሪክ ሰርቶ ለማለፍ በቁርጠኝነት እየሠራ ይገኛል -ከንቲባ አዳነች አቤቤ

አዲስ አበባ፤ የካቲት 12/2016(ኢዜአ)፦ የአሁኑ ትውልድ የአባቶቹን አኩሪ ገድል ከመዘከር ጎን ለጎን የራሱን ታሪክ ሰርቶ ለማለፍ በቁርጠኝነት እየሠራ እንደሚገኝ የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ተናግረዋል፡፡
87ኛው የየካቲት 12 መታሰቢያ መርሐ ግብር በአዲስ አበባ ስድስት ኪሎ የሰማዕታት ሃውልት በዛሬው እለት እየታሰበ ይገኛል።
የአዲስ አበበ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤና ሌሎች እንግዶች በ6 ኪሎ የሰማዕታት ሐውልት ስር የአበባ ጉንጉን አስቀምጠዋል።
ዛሬ እየታሰበ የሚገኘው የካቲት12 ቀን 1929 ዓ.ም የፋሺስት ጣልያን ወታደሮች ያደረሱትን አስከፊ ጭፍጨፋ ለማሰብ መሆኑ ተጠቁሟል።
በወቅቱም ከ30 ሺህ በላይ የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎች የተጨፈጨፉበት መሆኑ ተጠቅሷል።
የአዲስ አበበ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ በዚሁ ወቅት ያለፈውን ታረክ መሠረት አድርገን የበለጸገች ሀገር ለመገንባት እየሠራን ነው ብለዋል።
ስላለፈው ታሪክ ብቻ መናገር ዋጋ አይኖረውም ያሉት ከንቲባዋ የአሁኑ ትውልድ የአባቶቹን አኩሪ ገድል ከመዘከር ጎን ለጎን የራሱን ታሪክ ሰርቶ ለማለፍ በቁርጠኝነት እየሠራ መሆኑን ገልጸዋል።
የጥንታዊት ኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች ማህበር ፕሬዝዳንት ልጅ ዳንኤል ጆቴ መስፍን በበኩላቸው ኢትዮጵያውያን የጣሊያንን ወረራ በመቃወም ባደረጉት ተጋድሎ በአድዋ ጦርነት ድል መቀዳጀታቸውን ተናግረዋል።
በዚህም ቂም የያዘው የፋሽስት ኃይል በኢትዮጵያውያን ላይ ከፍተኛ በደል ለመፈጸም ዳግም ወረራ በማካሄድ ጭፍጨፋ መፈጸሙን አስታውሰዋል።
የፋሺስት ጣሊያን ጦር ለሦስት ቀናት በንጹሃን ኢትዮጵያውያን ላይ ጭፍጨፋ ማካሄዱን አስታውሰዋል።
ግፍና በደሉን አንቀበልም ካሉት መካከል አብርሃም ደቦጭና ሞገስ አስገዶም ግራዚያኒን በቦምብ ለመግደል ያደረጉትን ያልተሳካ ሙከራ ተከትሎ የግራዚያኒ ጦር የካቲት 12 ቀን 1929 ዓ.ም በኢትዮጵያዊን በተለይም በአዲስ አበባ ነዋሪዎች ላይ ዘግናኝ ጭፍጨፋ ማድረሱን ተናግረዋል።
በሰማዕታት መታሰቢያ በዓሉ ደማቸውን ለሃገር ክብር ላፈሰሱ፣ አጥንታቸውንም ለሕዝብ ነጻነት ለከሰከሱ ጀግኖች ሰማዕታት ክብር እንሰጣለን ብለዋል።
በሰማዕታት መታሰቢያ ስነ ስርዓቱ ከፍትኛ የመንግስት የስራ ኃላፊዎችና የጀግኖች አርበኞች ቤተሰቦች የተገኙ ሲሆን የተለያዩ አካላት የአበባ ጉንጉን አስቀምጠዋል።