ቀጥታ፡

በኢዜአ የተሰጠን የምስልና የድምፅ ቀረፃ ሥልጠና የተሻለ እውቀትና ክህሎት ያገኘንበት ነው- ሰልጣኞች

አዲስ አበባ፤ የካቲት 11/2016(ኢዜአ)፦ በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት(ኢዜአ) የተሰጠን የምስልና የድምፅ ቀረፃ ሥልጠና የተሻለ እውቀትና ክህሎት ያገኘንበት ነው ሲሉ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የኮርፖሬት ኮሙኒኬሽን ባለሙያዎች ገለጹ።

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የኮርፖሬት ኮሙኒኬሽን አመራሮችና ባለሙያዎች በኢዜአ ለአምስት ቀናት የተሰጣቸውን ሥልጠና አጠናቀዋል።

ከሰልጣኞቹ መካከል የኢትዮጵያ የኤሌክትሪክ ኃይል የሕዝብ ግንኙነትና የኮሙኒኬሽን ሥራ አስኪያጅ ፍስሃ ጌታቸው፤ የሥልጠና ቆይታችን ንድፈ-ሃሳብን ከተግባር ጋር ያቀናጀ በመሆኑ ጥሩ እውቀትና ክህሎት ያገኘንበት ነው ብለዋል።

ለተቋሙ ደንበኞች ወቅታዊና ትክክለኛ መረጃዎችን ተደራሽ ለማድረግ ጥራት ያለው የምስልና የድምፅ መረጃ የሚያስፈልግ በመሆኑ ለዚህ በቂ ግብአት አግኝተናል ነው ያሉት።

በመሆኑም ሥልጠናው ለቀጣይ ሥራችን ቅልጥፍና እና ጥራት የሚያግዙ አቅሞችን ፈጥሮልናል ብለዋል።


 

ሌላኛው ሰልጣኝ ሙሉጌታ ጉቱ፤ ከኅብረተሰቡ ምን ይጠበቃል? የተዘረጉ መሰረተ-ልማቶችን እንዴት መንከባከብና መጠበቅ አለብን? በሚለው ዙሪያ ሰፊ ግንዛቤ ለመፍጠር የሚያስችል ሥልጠና ስለመሆኑ ተናግረዋል።


 

በኢዜአ የሕዝብ ግንኙነትና ስትራቴጂያዊ አጋርነት ዳይሬክተር ዮሐንስ ወንድይራድ፤ ኢዜአ መረጃን ለሕዝብ ተደራሽ ከማድረግ ባለፈ ለሀገር ገጽታ ግንባታና የጋራ መግባባት የላቀ አበርክቶውን እየተወጣ መሆኑን ገልፀዋል።

ለተለያዩ ተቋማት የተግባቦትና የሙያ ሥልጠናዎችን በመስጠት የመረጃ ተደራሽነትን ለማሳለጥ እገዛ እያደረገ መሆኑን ጠቁመው፤ በቀጣይም አጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም