በአፍሪካ ዘመኑን የሚመጥን፣ ዘላቂና ሁሉን አካታች የትምህርት ሥርዓት መዘርጋትና በትብብር መሥራት ይገባል- ዶክተር ኤርጎጌ ተስፋዬ - ኢዜአ አማርኛ
በአፍሪካ ዘመኑን የሚመጥን፣ ዘላቂና ሁሉን አካታች የትምህርት ሥርዓት መዘርጋትና በትብብር መሥራት ይገባል- ዶክተር ኤርጎጌ ተስፋዬ
አዲስ አበባ፤ የካቲት 11/2016(ኢዜአ)፦በአፍሪካ ዘመኑን የሚመጥን፣ ዘላቂና ሁሉን አካታች የትምህርት ሥርዓት መዘርጋትና በትብብር መሥራት ያስፈልጋል ሲሉ የሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ኤርጎጌ ተስፋዬ ገለጹ።
ከ37ኛው የአፍሪካ ሕብረት የመሪዎች ጉባዔ ጎን ለጎን ለሦስት ቀናት የተካሄደው የአፍሪካ ወጣት መሪዎች ጉባዔ ተጠናቋል።
ጉባዔው ከኢፌዴሪ የሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ ከኢትዮጵያ ወጣቶች ምክር ቤት እና ከፓን- አፍሪካ የወጣቶች ሕብረት ጋር በመተባበር የተዘጋጀ ነው።
በጉባዔው ላይ ንግግር ያደረጉት የሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ኤርጎጌ ተስፋዬ፤ ለአፍሪካ ወጣቶች ዘመኑን የሚመጥን ጥራት ያለው ትምህርት ተደራሽ ማድረግ ይገባል ብለዋል።
የ21ኛውን ክፍለ ዘመን የሚመጥን የትምህርት ሥርዓት በመገንባትና ተደራሽ በማድረግ የአፍሪካን ብልፅግና ማረጋገጥ ተገቢ መሆኑን አንስተዋል።
በአህጉሪቷ ዘላቂ ሰላምና ቀጣይነት ያለው እድገት ለማምጣት የትምህርት ጥራትና ተደራሽነት ወሳኝ በመሆኑ ለወጣቶችና ታዳጊዎች የትምህርት ዕድሎችን ማመቻቸት ይገባል ብለዋል።
በዚህ ረገድ ኢትዮጵያ ከቀጣናው አገራት ጋር ይበልጥ ትስስርና ትብብር በመፍጠር እየሰራች መሆኑን ሚኒስትሯ ገልፀዋል።
የአፍሪካ ወጣቶች ሕብረት የምስራቅ አፍሪካ ምክትል ፕሬዝዳንት ሙታሲ ኦሊቨር፤ በአፍሪካ ዘመኑን የሚመጥን፣ ዘላቂና ሁሉን አካታች የትምህርት ሥርዓት መዘርጋት የሚያስፈልግበት ጊዜ ላይ እንገኛለን ብላለች።
የኢትዮጵያ ወጣቶች ሕብረት ምክትል ፕሬዝዳንት ዮሱፍ መሐመድ፤ የወጣቶች ጉባዔ የወጣቶችን ሁለንተናዊ ችግር መፍታት የሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ በማተኮር ውጤታማ ውይይት ማድረጉን ጠቁሟል።
የካሜሮን ወጣቶች ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ፋሲሙቶ ኢያዋ በበኩሏ፤ በጉባዔው ለአህጉሪቱ ዘርፈ-ብዙ ችግሮች መፍትሔ የሚያመላክቱ ጠቃሚ ውይይቶች መደረጋቸውን አንስታለች።