ቀጥታ፡

የእናቶችና የህፃናት ጤና ለመጠበቅ የሚሰሩ ተግባራት ውጤታማ ለማድረግ የባለድርሻ አካላት ትብብር ሊጠናከር ይገባል  

አዲስ አበባ፤ የካቲት 11/2016(ኢዜአ)፦ የእናቶችና የህፃናት ጤና ለመጠበቅ የሚሰሩ ተግባራት ውጤታማ ለማድረግ የዘርፉ ባለድርሻ አካላት የነቃ ተሳትፎ ሊያደርጉ እንደሚገባ የጤና ሚኒስቴር ገለጸ።  

የኢትዮጵያ የፅንስና የማህፀን ሐኪሞች ማኅበር ለሁለት ቀናት የሚቆይ ዓመታዊ ጉባዔውን በማካሄድ ላይ ይገኛል።

በጉባዔውም በጤናው ዘርፍ ላይ ያሉ ባለሙያዎችን የአመራርነት ሚናቸውን በማጎልበት የእናቶችንና የጨቅላ ህፃናትን ጤናማነት ማረጋገጥ በሚቻሉባቸው ርዕሰ-ጉዳዮች ምክክር እየተደረገ ነው።

የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር አየለ ተሾመ በዚሁ ጊዜ እንዳሉት፤ መንግሥት በጤናው ዘርፍ ትኩረት ሰጥቶ ከሚሰራባቸው አንኳር ጉዳዮች ውስጥ የእናቶችና የህፃናት ጤና አንዱ ነው።

ሚኒስቴሩ በዚህ ረገድ የእናቶችንና የህፃናትን ሕይወት ከሞት ለመታደግ የሚያስችሉ ዘርፈ-ብዙ ተግባራት ባለድርሻ አካላትን ያሳተፈ ሥራ በማከናወን ላይ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

ከእነዚህም መካከል በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች የጤና ኤክስቴንሽን ተግባርን በማጠናከር ሕብረተሰቡ   ስለ እናቶች ጤና አገልግሎት ያለውን ግንዛቤ ማሳደግና በጤና ተቋማት የሕክምና አገልግሎት የማግኘት ፍላጎታቸው እንዲጠናከር አስተዋፅዖ አድርጓል ነው ያሉት።

ይህም ማኅበረሰቡ ለእናቶችና ህፃናት ጤና መጠበቅ የመፍትሔው አካል የሚሆኑበትን አቅም ፈጥሯል  ሲሉ አክለዋል።

በተጨማሪም ሴቶች ከእርግዝና ጋር በተያያዘ ወደ ጤና ተቋማት በወቅቱ እንዲመጡ የትራንስፖርት አገልግሎት ምቹ እንዲሆን የማስቻል፣ በዘርፉ ላይ ያሉ የህክምና ሙያተኞችን የማብቃትና ግብዓት የማሟላት ሥራም እንደዚሁ ተጠቃሽ ናቸው ሲሉ አክለዋል።

የሴቶችና የህፃናት ሞትን ለመቀነስ  የሕክምና ባለሙያዎች በሚሰጡት ሙያዊ አገልግሎት ብቻ በቂ አለመሆኑን ገልጸው፤ ሙያተኞቹን የአመራር ሚናቸውን በማሳደግ ለኅብረተሰቡ ተደራሽ የሆነ ቀልጣፋ አገልግሎት መስጠት ተገቢ በመሆኑ ትኩረት ሰጥተን ልንሰራ ይገባል ብለዋል።

ከዚህ አንፃር የኢትዮጵያ የፅንስና ማህፀን ሐኪሞች ማኅበር የእናቶችና የህፃናትን ጤና ለመጠበቅና ዘርፉን ለማዘመን የሚሰራቸውን ሥራዎች አጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል ነው ያሉት። 

በተለይም በሀገሪቱ የእናቶችና የህፃናትን ጤና ለመጠበቅ የሚሰሩ ተግባራት ውጤታማ እንዲሆን በዘርፉ ላይ ያሉ ባለድርሻ አካላት የነቃ ተሳትፎ ሊያደርጉ እንደሚገባ አፅንዖት ሰጥተዋል።


 

የኢትዮጵያ የፅንስና የማህፀን ሐኪሞች ማኅበር ፕሬዝዳንት ዶክተር አብዱልፈታህ አብዱልቃድር በበኩላቸው፤ ማኅበሩ ላለፉት 32 ዓመታት በእናቶችና ጨቅላ ህፃናት ከሞት ለመታደግ  የሚያስችሉ ተግባራትን በማከናወን ላይ ይገኛል ብለዋል።

ለአብነትም ማኅበሩ ከተለያዩ ባለድርሻና አጋር አካላት ጋር በመሆን በማህፀንና ፅንስ ላይ የሚሰሩ የሕክምና ባለሙያዎችን አቅም የማጎልበት፣ ሙያዊ ሥነ-ምግባር በተገቢው እንዲተገበር የማድረግና የኅብረተሰቡን ግንዛቤ ማሳደግ ተጠቃሽ መሆኑን ጠቁመዋል።

በተጨማሪም በአገሪቱ ጤና ዘርፍ ለማሳደግ የሚያስችሉ ለፖሊሲ ግብዓት የሚሆኑ ምክረ-ኃሳቦችን   በተለያዩ  ጊዜያት ለሚመለከታቸው አካላት እንደሚያቀርብ ተናግረዋል።

እንደ አገር የእናቶችንና የህፃናትን ጤና አጠባበቅ ለማሻሻል በዘርፉ ላይ የሚገኙ ሙያተኞችን የአመራርነት አቅማቸውን ማጎልበት ትልቅ ድርሻ አለው ብለዋል።

ይህንንም መነሻ በማድረግ ማኅበሩ በጤናው ዘርፍ ላይ ያሉ ባለሙያዎችን የአመራርነት ሚናቸውን በማጎልበት የእናቶችንና የጨቅላ ህፃናትን ጤናማነት ማረጋገጥ በሚቻሉባቸው ርዕሰ-ጉዳዮች ላይ የጀመራቸውን ተግባራት አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ገልፀዋል።


 

የዓለም አቀፉ የፅንስና ማህፀን ሐኪሞች ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት ፕሮፌሰር አኔ ኪሃራ በበኩላቸው፤ በኢትዮጵያ  የእናቶችን ሞት ለመቀነስ በርካታ የተሰሩ ሥራዎች የሚበረታቱ መሆናቸውን ተናግረዋል።

ይሁን እንጂ የእናቶችን የህፃናትን ጤና ለመጠበቅ የሚሰሩ ተግባራቶች ውጤታማ እንዲሆኑ፤ ዘርፉን በብቃት መምራት የሚችል ብቁ የፅንስና የማህፀን ሐኪም ሙያተኞችን ማፍራት ያስፈልጋል ብለዋል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም