ቀጥታ፡

የኩመር አውላላ ስደተኞች ሳይት አዲስ ከሱዳን የመጡ ስደተኞችን መቀበሉን አስታወቀ

መተማ፤ የካቲት 11/2016 (ኢዜአ)፤ በምዕራብ ጎንደር ዞን መተማ ወረዳ በኩመር አውላላ ስደተኞች ሳይት ከሦስት ሺህ በላይ  አዲስ ከሱዳን የመጡ ስደተኞች መቀበሉን   የኢትዮጵያ የስደተኞችና ተመላሾች አገልግሎት አስታወቀ።

በኢትዮጵያ ስደተኞችና ተመላሾች አገልግሎት የኩመር አውላላ ስደተኞች ሳይት አስተባባሪ አቶ ታምራት ደምሴ እንደተናገሩት፤ በመተማ በኩል ከ22 ሺህ በላይ ስደተኞች ህጋዊ ምዝገባ አሟልተው ወደ ኢትዮጵያ ገብተዋል።

ሱዳናውያን፣ ኤሪትራውያንና የሌሎች አገር ስደተኞች መግባታቸውን ተናግረዋል።

አገልግሎቱ ከዚህ በፊት ከነበረው በተጨማሪ አሁን በመተማ ወረዳ 24 ሄክታር መሬት ተረክቦ መጠለያ ጣቢያ መመስረቱን ጠቁመዋል።

አዲስ የተመሰረተው ጣቢያ ከ15 ሺህ በላይ ስደተኞችን ማስተናገድ የሚችል ሲሆን፤ አሁን ወደ ኢትዮጵያ ለመግባት እየተጠባበቁ ካሉ ሦስት ሺህ ስደተኞች መካከል ከ900 በላይ የሚሆኑትን መቀበሉን ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ ለተቸገሩት ሁሉ ድንበሯን ክፍት በማድረግ ዓለምአቀፍ የሰብዓዊ ድጋፍ እያደረገች መሆኑን አብራርተዋል።

በዞኑ የመተማ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ደሳለኝ ሞገስ  አስተዳደራቸው  ለስደተኞች መጠለያ የሚውል 46 ሄክታር መሬት አዘጋጅቷል ብለዋል።

የኩመር መጠለያ ጣቢያ 22 ሄክታር የሚሸፍን ሲሆን፤ ይህም ነባር  ከስምንት ሺህ በላይ ስደተኞችን መያዙን ጠቁመዋል። 

በአዲስ የተሰጠው 24 ሄክታር መሬት አውላላ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ የሚገኝ መሆኑን ገልጸው የአካባቢው ማህበረሰብ በእንግዳ ተቀባይነት ባህሉ መሰረት ስደተኞችን ተቀብሎ እያስተናገደ ነው ብለዋል።

በወረዳው የኩመር አውላላ ቀበሌ ነዋሪ አቶ መልኬ ገበየ በበኩላቸው፤ በስደት የመጡ ሱዳናውያንን ለመደገፍና ደህንነታቸውን ለመጠበቅ መዘጋጀታቸውን ገልፀዋል።

የሞቀ ቤታቸውን ጥለው የመጡ የተቸገሩ ወገኖችን  መደገፍ ባህላችን በመሆኑ በመልካምነት ተደጋግፈው እንደሚኖሩ  አብራርተዋል።

ከካርቱም ሸርደፊያ አካባቢ አምስት ሕጻን ልጆቻቸውን ይዘው መምጣታቸውን የገለፁት ደግሞ ሳድያ አደም ናቸው።

"ከዚህ በፊት በነበረን መረጃ መሰረት ሰው አክባሪና አዛኝ ልብ ያለው የኢትዮጵያ ማህበረሰብ በተግባር አይተናል" ብለዋል።

በአገራቸው ባጋጠመ ችግር ከመኖሪያ ቀያቸው ቢፈናቀሉም ኢትዮጵያውያን ላደረጉላቸው አቀባበል አመስግነዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም