ከተሳሳተ ትርክት ነጻ ሆነን በጋራ በመስራት ለኢትዮጵያ ብልጽግና ስኬት እንሰራለን-ወጣቶች - ኢዜአ አማርኛ
ከተሳሳተ ትርክት ነጻ ሆነን በጋራ በመስራት ለኢትዮጵያ ብልጽግና ስኬት እንሰራለን-ወጣቶች
ሚዛን አማን፤የካቲት 11/2016(ኢዜአ)፡-ከተሳሳተ ትርክት ነጻ በመሆንና በጋራ በመሥራት ለኢትዮጵያ ብልጽግና ስኬት የበኩላቸውን እንደሚወጡ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ወጣቶች ገለጹ።
ወጣቶቹ ትላልቅ ሀገራዊ ፕሮጀክቶችና ብሔራዊ ጥቅምን ለማስከበር እየተሠሩ ያሉ ሥራዎች ለነገ ሁለንተናዊ ዕድገት ተስፋ ሰጪ መሆናቸውንም ለኢዜአ ተናግረዋል።
በክልሉ ዳውሮ ዞን የሚኖረው ወጣት አሸናፊ በየነ እንዳለው፤ የኢትዮጵያ የዕድገት ጉዞ በህዝብና በመንግስት ትብብር ተጠናክሮ እንዲቀጥል ነጠላ ትርክቶችን ወደ ጎን መተው ይገባል።
የክልሉ ወጣቶች ከተሳሳተ ትርክት ነጻ ሆነው በጋራ በመሥራት የኢትዮጵያን ብልጽግና እውን ለማድረግ የበኩላችንን ልንወጣ ይገባል ሲልም ነው የገለጸው።
ሀገራዊ የለውጥ ጉዞው ለወጣቶች ይዞት የመጣውን ዕድል በአግባቡ በመጠቀም ራስን ለመለወጥና የሀገርን እድገት ለማረጋገጥ ተግቶ መስራት እንደሚገባም ተናግሯል።
በተለይ ለራሳቸው ጥቅም ሲሉ የግል አጀንዳቸውን ሀገራዊ በማስመሰል ወጣቱን ለጥፋት ለሚያነሳሱ አካላት ጆሮ ባለመስጠት የተጀመረውን የለውጥ ጉዞ ለማስቀጠል ጠንክሮ እንደሚሰራም ገልጿል።
ወጣቱ ሀገርና ህዝብን ማገልገል እንጂ በሀሰተኛ ትርክት ተነሳስቶ አንድነትን ወደሚያፈርስ ተግባር መግባት እንደሌለበትም መክሯል።
"የሀገርን ሉዓላዊነት ለማስቀጠልና ዕድገትን ለማፋጠን እንደ ወጣት በአባቶቻችን ሀገራዊ ፍቅር በሰላም እና በልማት ጠንክረን መስራት አለብን" ያለችው ደግሞ ከሸካ ዞን የመጣችው ወጣት ሳይሉሽ ግዛው ናት።
"የበለጸገች ኢትዮጵያን እውን ለማድረግ ለአለመግባባት ምክንያት የሆኑ ነጠላ ትርክቶችን በመተው አንድ የሚያደርጉንን ማጉላት"ይባል ያለችው ወጣቷ፤ እንደወጣት ለልማትና ለፈጠራ እሳቤ ትኩረት መስጠት ይገባል ብላለች።
ሁሌም ለሰላም፣ ለአብሮነት እና ለልማት ቅድሚያ መስጠት ከተቻለ ሀገር ያላት ሀብት ለሁላችንም ይበቃል ስትልም አክላለች።
ከካፋ ዞን የመጣው ወጣት ወንድማገኝ ከበደ በበኩሉ እንደ ሀገር ፊታችንን ሙሉ ለሙሉ ወደልማት ካዞርን በቅርቡ ሀገራዊ እድገትን ማረጋገጥ እንደሚቻል የተጀመሩ የተለያዩ ፕሮጀክቶች ያሳያሉ ብሏል።
ከልማት ፕሮጀክቶች ባሻገር በዲፕሎማሲ ዘርፍ እየተገኙ ያሉ ድሎች ብሔራዊ ጥቅምን የሚያስጠብቁ መሆናቸውንም ተናግሯል።
በተለይ ኢትዮጵያ የባህር በር እንዲኖራት እየተደረገ ያለው ጥረት ውጤታማ እንዲሆን ከመንግስት ጎን በመሆን የበኩሉን እንደሚወጣ አረጋግጧል።
ለሚመጣው ትውልድ የሚተርፉ ሥራዎችን ሠርቶ ለማለፍ የሚደረገው ጥረት እንደ ሀገር ውጤታማ እንዲሆን ሁሉም ጠንክሮ መሥራት እንዳለበትም አመልክቷል።
"እኔ ለሀገሬ ሰላም ዘብ ነኝ" በሚል መሪ ቃል በሰላምና ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ወጣቶች ሊኖራቸው ስለሚገባ ሚና ላይ ያተኮረ የውይይት መድረክ በሚዛን አማን ከተማ መካሄዱ ይታወሳል።