ኢዜአ የተደራሽነት አድማሱን በማስፋት ከኢትዮጵያ አልፎ የአፍሪካ አስተማማኝ የዜና ምንጭ መሆን አለበት- አቶ ተስፋዬ ቤልጂጌ

418

አዲስ አበባ ፤ የካቲት 10/2016(ኢዜአ)፦የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት /ኢዜአ/ የተደራሽነት አድማሱን በማስፋት ከኢትዮጵያ አልፎ የአፍሪካ አስተማማኝ የዜና ምንጭ መሆን አለበት ሲሉ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግስት ዋና ተጠሪ ሚኒስትር ተስፋዬ ቤልጂጌ ገለጹ።

የመንግስት ዋና ተጠሪ ሚኒስትሩ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት /ኢዜአ/ ያስገነባውን ዘመናዊ የሚዲያ ኮምፕሌክስ ጎብኝተዋል።

ከጉብኝቱ በኋላ በሰጡት አስተያየትም ኢዜአ ከኢትዮጵያም አልፎ በአፍሪካ የገዘፈ ታሪክና ስም ያለው ተቋም መሆኑን ገልጸዋል። 

በመሆኑም አዲስ ያስገነባው ዘመናዊ የሚዲያ ኮምፕሌክስ የተቋሙን ራእይና ተልእኮ ለማሳካት ወሳኝ መሆኑን ጠቅሰው ለኢትዮጵያ የሚዲያ ኢንዱስትሪ እድገትም ጥሩ መሰረት መሆኑን ጠቅሰዋል።


 

የተገነባው የሚዲያ ኮምፕሌክስና እየተጠቀመ ያለው ቴክኖሎጂ ከዓለም ትላልቅ መገናኛ ብዙሃን ጋር የሚስተካከል መሆኑንም ገልጸዋል።

በመሆኑም ኢዜአ በቋንቋ ብዝሃነትም ይሁን ተቋማዊ አቅም የተደራሽነት አድማሱን በማስፋት ከኢትዮጵያ አልፎ የአፍሪካ አስተማማኝ የዜና ምንጭ መሆን አለበት ነው ያሉት። 

በሁሉም ዘርፍ በሀገሪቷ የተከናወኑ የሪፎርም ስራዎች ውጤታማ መሆናቸውን ጠቅሰው ለሚዲያው የሪፎርም ስራም ኢዜአ ሁነኛ ማሳያ ነው ብለዋል።

በኢትዮጵያ የዴሞክራሲ ስርአት እንዲጎለብት በማድረግ ረገድ የሚዲያ ሚና ወሳኝ መሆኑን የገለጹት አቶ ተስፋዬ፤ ኢዜአ ይህንን ሚናውን በመወጣትና ብሄራዊ መግባባት በመፍጠር የጀመራቸውን ስራዎች አጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ገልጸዋል።

በኢትዮጵያ ሁለንተናዊ ልማት ተረጋግጦ የተጀመረው የብልጽግና ጉዞ እንዲሳካ በመስራት ረገድ ትልቅ ሀገራዊ ሃላፊነት ያለበት መሆኑንም አንስተዋል።

ኢዜአ የስርጭትና ተደራሽነት አድማሱን በምስራቅ አፍሪካ ለማስፋት በኬንያ እና በጅቡቲ ቅርንጫፎችን ለመክፈት በዝግጅት ላይ ይገኛል።

ከተመሠረተ 82 ዓመታት የሆነው አንጋፋው ኢዜአ ብሔራዊ መግባባት የመፍጠርና የአገር ገፅታ ግንባታ ተልዕኮውን ለማሳካት ዜና እና ዜና ነክ መረጃዎችን ተደራሽ በማድረግ ላይ ይገኛል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም