ዛምቢያ ከኢትዮጵያ ጋር በቴሌኮሚኒኬሽንና በቱሪዝም መስክ በትብብር ለመስራት ጽኑ ፍላጎት አላት- የሀገሪቷ የቴክኖሎጂ እና ሳይንስ ሚኒስትር ፍሌሲ ሙታቲ - ኢዜአ አማርኛ
ዛምቢያ ከኢትዮጵያ ጋር በቴሌኮሚኒኬሽንና በቱሪዝም መስክ በትብብር ለመስራት ጽኑ ፍላጎት አላት- የሀገሪቷ የቴክኖሎጂ እና ሳይንስ ሚኒስትር ፍሌሲ ሙታቲ
አዲስ አበባ ፤ የካቲት 10/2016(ኢዜአ)፦ ዛምቢያ ከኢትዮጵያ ጋር በቴሌኮሚኒኬሽን፣ በቱሪዝምና በቆዳ ኢንዱስትሪ መስክ በትብብር ለመስራት ጽኑ ፍላጎት እንዳላት የዛምቢያ የቴክኖሎጂ እና ሳይንስ ሚኒስትር ፍሌሲ ሙታቲ ተናገሩ።
በአፍሪካ ሕብረት የመሪዎች ጉባዔ የታደሙት የዛምቢያ የቴክኖሎጂ እና ሳይንስ ሚኒስትር ፍሌሲ ሙታቲ ለኢዜአ እንዳሉት፣ የሕብረቱ ትኩረት ዘመኑን በሚዋጅ ትምህርት ትግበራ ላይ ማተኮሩ የሚደነቅ ነው።
በአፍሪካ ዘመኑን የሚመጥን ትምህርት ስርዓት ለመገንባት ጥራት፣ ተደራሽነት እና ውጤታማነት ወሳኝ መለኪያዎች እንደሆኑ ገልጸዋል።
ይህን ዕውን ለማድረግ የትምህርት መሰረተ ልማት መገንባት፣ የትምህርት ማህበረሰቡን በክህሎት ማብቃት፣ በቴክኖሎጂ መደገፍ ብሎም የተማረና ስራ ፈጣሪ ወጣት ማፍራት ላይ በትኩረት መስራት እንደሚጠይቅ ገልጸዋል።
ዛምቢያ በቀጣይ ዓመት የፈጠራ ባለተሰጥኦ አፍሪካዊያን ዓለም አቀፍ ውድድር እንደምታስታናግድ ገልጸው፣ የሕብረቱ ትኩረት ትምህርት መሆኑ ትልቅ እድል ነው ብለዋል።
ኢትዮጵያ እና ዛምቢያ በበርካታ ኢኮኖሚ መስኮች መተባበር እንደሚችሉ ገልጸው፣ ለአብነትም ኢትዮጵያ በቴሌኮሚኒኬሽን መሰረተ ልማት ከዛምቢያ በላቀ ደረጃ የተራመደች አገር መሆኗን ጠቅሰዋል።
በዚህም ዛምቢያ በቴሌኮሚኒኬሽን ዘርፍ ከኢትዮጵያ ልምድ እና ዕውቀት ለመሸመት ጽኑ ፍላጎት እንዳላት እና ልዑካቸውም በዚህ ጉዳይ ላይ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ለመነጋገር ዝግጁ እንደሆነ ጠቁመዋል።
ሰባተኛው አስደናቂ ሀብት (ቪክቶሪያ ሐይቅ) ባለቤቷ ዛምቢያ፣ ከስምንተኛው አስደናቂ የዓለም ቅርስ (ላሊበላ አብያተ ክርስቲያናት) ባለቤት ከሆነችው ኢትዮጵያ ጋር በቱሪዝም መስክ አብራ ለመስራት ፍላጎት እንዳላት ገልጸዋል።
ኢትዮጵያና ዛምቢያ ዕምቅ የቱሪዝም አቅም ያላቸው ሀገራት እንደሆኑ ገልፀው፤ በዘርፉ ልምድና ዕውቅት በመለዋወጥ በትብብር መስረት እንደሚያስችላቸው ነው ያነሱት።
ከዚህ ባለፈ ኢትዮጵያ በቆዳ ውጤቶች የተሻለ ስራ እየሰራች መሆኗን አድንቀው ዛምቢያ በዚህ ረገድ በጋራ መስራት እንደምትፈልግም ተናግረዋል።