የበለፀገች አፍሪካን እውን ለማድረግ ለአህጉራዊ ድንበር የለሽ ዲጂታላይዜሽን ትኩረት መስጠት ይገባል

375

አዲስ አበባ፤ የካቲት 9/2016(ኢዜአ)፦ በ2063 የበለፀገች አፍሪካን እውን ለማድረግ የተያዘውን ግብ ለማሳካት ለአህጉራዊ ድንበር የለሽ የቴክኖሎጂ ትስስርና ለአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ትኩረት መስጠት እንደሚገባ ተገለጸ።

"የዲጂታላይዜሽን መስፋፋት ለአፍሪካ ትራንስፎርሜሽን" በሚል መሪ ሃሳብ ላይ ያተኮረ የመንግሥታትና የተቋማት መሪዎች ውይይት በዓድዋ ድል መታሰቢያ ፓን-አፍሪካ አዳራሽ ተካሂዷል።

ፕሬዝዳንት ሣህለወርቅ ዘውዴ በዚህ ወቅት እንዳሉት፤ በፍጥነት እያደገ የመጣው የቴክኖሎጂ ምህዳር ዓለም ጂኦ-ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ማኅበረሰባዊ እና ባህላዊ ለውጦችን እንድታስተናግድ አስገድዷታል።


 

አፍሪካም ለዲጂታልና ለቴክኖሎጂ ፈጠራ ትኩረት እንድትሰጥ ጫና ማሳደሩንም ጠቅሰዋል።

አፍሪካ ዲጂታላይዜሽንን በማስፋፋት፣ ምርታማነትን በማሳደግ፣ ፈጠራን በማጎልበትና የሥራ ዕድልን በመጨመር ግዙፍ የኢኮኖሚ እድገት እንድታስመዘግብ ዕድል ይፈጥራል ነው ያሉት።

በ2063 የምንመኛትን የበለፀገች አፍሪካ ለመፍጠር የዲጂታላይዜሽን መስፋፋት ጉልህ ሚና እንደሚኖረው ጠቅሰው፤ ከ2020 እስከ 2030 የሚተገበር አህጉራዊ የዲጂታል ሽግግር አጀንዳ ወደ ሥራ መግባቱን አውስተዋል።

ኢትዮጵያም ከአህጉሪቱ እሳቤዎች ጋር የሚጣጣም ዲጂታል 2025ን ስትራቴጂ በማዘጋጀት ወደ ሥራ መግባቷን ጠቅሰዋል።

በዚህም የቴሌኮም መሠረተ-ልማት ማስፋፋት፣ የኢንተርኔት ተደራሽነትና አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ላይ ሰፋፊ ተግባራት እያከናወነች መሆኑን ገልፀዋል።

በአፍሪካ አካታችና ዘላቂ ልማትን ለማረጋገጥ የዲጂታል ሽግግርን ማፋጠን እንደሚገባም ጠቁመዋል።

በውይይት መድረኩ ላይ በዲጂታል አፍሪካ ዙሪያ ሃሳባቸውን ያካፈሉት የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ሥራ አስፈጻሚ ፍሬህይወት ታምሩ፤ የተሻለ ነገን በዘላቂነት ለመገንባት የቴክኖሎጂ አካታችነትን ማረጋገጥ ይገባል ብለዋል።

የአፍሪካ ሕብረት በአባል ሀገራት የሚተገበር ወሳኝ ስትራቴጂ መቅረጹን ጠቅሰው፤ ዛሬ ላይ በአህጉሪቱ 1 ነጥብ 4 ቢሊየን የሞባይል ተጠቃሚዎች እንዳሉና በ2030 1 ነጥብ 7 ቢሊየን ይደርሳል ተብሎ እንደሚጠበቅ ገልፀዋል።

በተለይም የፋይናንስ የትምህርትና የጤና ልማት አካታችነትን ለማረጋገጥ የሞባይል ቴክኖሎጂን መጠቀም ተገቢ እንደሆነ ጠቁመዋል።


 

በአፍሪካ ያልተነካውን የተፈጥሮ ኃብት ለማልማት የዲጂታል ተደራሽነት አስፈላጊ መሆኑን ገልፀዋል።

በዓለም የኢኮኖሚ ፎረም የአፍሪካ ቀጣና የትግበራ ቡድን ተባባሪ ሊቀመንበር ፕሮፌሰር ላንድሪ ሲኜ፤ አፍሪካ የኢኮኖሚ እድገትና መዋቅራዊ ለውጥን በማረጋገጥ በዓለም ተፅዕኖ ፈጣሪ ለመሆን ለዲጂታል አሠራር ትኩረት መስጠት እንዳለባት ተናግረዋል።

በአፍሪካ በርካታ አምራች ኃይል የመኖሩን ያህል የዲጂታል ልህቀት ያልዳበረበት ሥርዓተ-ምህዳር መኖሩንም ጠቅሰዋል።

በመሆኑም ለዲጂታላይዜሸን የቀረቡና የላቁ አፍሪካውያንን ለመፍጠር ከመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ጀምሮ ማስተማር ይገባል ነው ያሉት።

ይህም አምራች ኃይሉ በታዳጊነቱ የላቀ የቴክኖሎጂ ግንዛቤ እንዲኖረው ስለሚያደርግ ለኢኮኖሚ እድገት መፋጠን ወሳኝ እንደሆነም ጠቅሰዋል።

ኢትዮጵያ ቴክኖሎጂን በመጠቀም ሁሉን አቀፍ እድገትን ለማምጣት እየሰሩ ከሚገኙ ሀገራት መካከል ተጠቃሽ መሆኗንም ነው ፕሮፌሰሩ የተናገሩት።


 

የኢትዮጵያ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት ከፍተኛ አማካሪ ሰለሞን ካሳ፤ አፍሪካ በአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ (ሰው ሰራሽ አስተውሎት) ለውጥ ለማምጣት ኢትዮጵያ ሀገራዊ ሚናዋን ለመወጣት እየጣረች ነው ብለዋል።

ኢትዮጵያ ዲጂታል መር ኢኮኖሚ ለመገንባት የካፒታል ገበያ፣ የዲጂታል ክፍያ ሥርዓትን ጨምሮ ትኩረት መስጠቷን ተናግረዋል።

ያለንበት ዘመን የሰው ሰራሽ አስተውሎት እየተስፋፋ ያለበት ነው ያሉት አማካሪው፤ ይህ ዘርፍ በ2030 ለዓለም ኢኮኖሚ 12 ነጥብ 5 ትሪሊየን ዶላር እንደሚያበርክት ይጠበቃል ብለዋል።

ሆኖም አሁን ባለው ሂደት አፍሪካ የቴክኖሎጂ ኢ-ፍትሃዊ ተጎጂ በመሆኗ፤ ሀገራት ከፈጠራና ቴክኖሎጂ በአግባቡ ለመጠቀም የተባበረ ጥረት እንዲያደርጉም ጠቁመዋል።

የኦንአፍሪቅ የዲጂታል ክፍያ መፈጸሚያ ድርጅት መሥራችና ዋና ሥራ አስፈጻሚ ዳሬ ኦኮጁ በበኩላቸው፤ በአፍሪካ ቴክኖሎጂ ጥቅም ላይ ቢውል አህጉራዊ ብልፅግናን በአጭር ጊዜ ማረጋገጥ እንደሚቻል ጠቁመዋል።

በአፍሪካ ለአነስተኛና መካከለኛ የቢዝነስ ተቋማት ዲጂታላይዜሽን መስፋፋት ድንበር የለሽ የቴክኖሎጂ ትስስርን ማጠናከር ተገቢ ነው ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም