የአድዋ ድል መታሰቢያ ሙዚየም የኢትዮጵያ ድል በአፍሪካ ታሪክ ጉልህ ስፍራ እንዳለው ማሳያ ነው

1377

አዲስ አበባ፤ የካቲት 9/2016(ኢዜአ)፡- የአድዋ ድል መታሰቢያ ሙዚየም የኢትዮጵያን ድል የሚዘክር እና ድሉ በአፍሪካ ታሪክ ውስጥ አገሪቱ ያላትን ጉልህ ስፍራ የሚያሳይ መሆኑ ተገለጸ።

የዓድዋ ድል ኢትዮጵያውያን 128 ዓመታት በፊት በአንድነት ተሰልፈው ድል በመንሳት ነፃነታቸውን ያስከበሩበት መሆኑን  ሩሲያ የዜና አገልግሎት ስፑትኒክ ዘግቧል።

ስፑትኒክ የአድዋ ድል መታሰቢያ ሙዚየም ምረቃን አስመልክቶ ከአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አማካሪ ልደት ሙለታ ጋር ቃለምልልስ አድርጓል። በዚሁ ቃለምልልስ ላይ ልደት ሙለታ ሙዚየሙ በመሀል አዲስ አበባ ላይ እንዲገነባ የተወሰነው ቦታው ለመላው ኢትዮጵያውያን ካለው ታሪካዊ ፋይዳ አንጻር መሆኑን አስረድተዋል።

ሙዚየሙ የተገነባበት ቦታ ኢትዮጵያውያን ወደ አድዋ ከመዝመታቸው በፊት ከሁሉም የአገሪቱ አቅጣጫዎች በመትመም የተሰበሰቡበት መሆኑን አማካሪዋ አስገንዝበዋል። መታሰቢያ ሙዚየሙ  የኢትዮጵያውያን የአንድነት ምልክት ሆኖ ከማገልገሉም በተጨማሪ የአድዋ ድል መነሻ መሆኑንም ያሳያል ብለዋል።

በዚህ ታሪካዊ የአDዋ ድል መታሰቢያ ሙዚየም በርካታ ታሪካዊ ቅርሶች የያዘ መሆኑን ያስረዱት ልደት ሙለታ ከእነዚህ መካከል በጠንካራ ዲፕሎማሲያዊ ጥረት ከተሰረቀበት ጣሊያን አገር እንዲመለስ የተደረገው እ.አ.አ 1935 ኢትዮጵያውያን ከጀርመን ኢንጂነሮች ጋር በመተባበር የሰሩት የመጀመሪያ የኢትዮጵያ አውሮፕላን እንደሚገኝበት አስረድተዋል።

አማካሪዋ ከአድዋ ድል መታሰቢያ ሙዚየም መገንባት ማዕከላዊ ሀሳቦች መካከል አንዱ ኢትዮጵያ በቅኝ ግዛት ወረራ ያሳየችውን ተቃውሞና አልገዛም ባይነት ለማስታወስ እና የሀገሪቱን ድልመዘከር ነው ብለዋል።

ሁሉን አቀፍና አካታች የሆኑ ቀጠናዊና ዓለም አቀፋዊ ትብብሮችን በስፋት መጠቀም እንደሚያስፈልግ ያብራሩት አማካሪዋ ጂኦ ፖለቲካል አሰላለፎችን በመገንዘብ የታዳጊ ሀገራትን ድምጽ የሚያጎሉ ቁልፍ ዓለም አቀፍ መድረኮችን መጠቀም እንደሚገባም ጠቁመዋል።

አማካሪዋ አክለውም፤ ኢትዮጵያ በቅርብ ጊዜ ብሪክስ (BRICS) ውስጥ በአባልነት መካተቷ በአለም አቀፍ ዲፕሎማሲ እና በአለም ዙሪያ ካሉ አገራት ጋር በሚደረገው የትብብር ሂደት እያደገ የመጣውን ተጽእኖ ፈጣሪነቷ ያሳያል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም