ቀጥታ፡

የበለፀገች አፍሪካን እውን ለማድረግ በትምህርት ዘርፍ  በጋራ መሥራት ይገባል...የወቅቱ የአፍሪካ ሕብረት ሊቀመንበር 

አዲስ አበባ፤ የካቲት 9/2016 (ኢዜአ)፡ የበለፀገች አፍሪካን እውን ለማድረግ በትምህርት ዘርፍ አገራቱ በጋራ ሊሰሩ እንደሚገባ የወቅቱ የአፍሪካ ሕብረት ሊቀመንበር ሞሃመድ ኦውልድ ኤል ጋዞኒ  ገለጹ።

37ኛው የአፍሪካ ሕብረት የመሪዎች ጉባዔ ዛሬ በሕብረቱ ዋና መቀመጫ አዲስ አበባ የተጀመረ ሲሆን፤ ሞሪታኒያ የአፍሪካ ሕብረት ሊቀመንበርነትን ከኮሞሮስ በይፋ ተረክባለች።

በጉባዔው መክፈቻ ላይ ንግግር ያደረጉት የወቅቱ ሊቀመንበር  ሞሃመድ ኦውልድ ኤል ጋዞኒ  ከአህጉሪቷ ሕዝብ 62 በመቶ የሚሆነው ወጣት ነው ብለዋል።

ይህን የወጣት ኃይል በማስተማርና  በማሰልጠን የሚጠበቀውን ውጤት ማስመዝገብ የሁሉም አገራት ኃላፊነት ነው ብለዋል።

በዚህም የአጀንዳ 2063ን ግቦች ለማሳካትና የበለፀገች አፍሪካን እውን ለማድረግ ከምንጊዜም በላይ ዜጎችን በማስተማር ተወዳዳሪና ብቁ ለማድረግ በቁርጠኝነት መሥራት እንደሚጠበቅ ተናግረዋል።

በሌላ በኩል የአፍሪካ ነፃ የንግድ ቀጣና ትግበራን በሚጠበቀው ልክ ለማፋጠን የተጀመሩ ጥረቶች ተጠናክረው መቀጠል ይኖርባቸዋል ብለዋል።

በዚህም አፍሪካን በመሠረተ-ልማት የማስተሳሰር ተግባራት በትኩረት ሊተገበሩ የሚገባቸው መሆኑን አንስተዋል።

በአህጉሪቱ ስጋት የሆነው የሰላም እጦትንና ግጭቶችን በዘላቂነት ለመፍታትም አፍሪካውያን ቁጭ ብለው በመነጋገርና በዲፕሎማሲያዊ አካሄድ ችግሮችን በራስ አቅም ለመፍታት የሚያስችል ስልት ሊከተሉ እንደሚገባ አክለዋል።

የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የአየር ንብረት ለውጥ ፈተናን ለመጋፈጥ የሚያስችል ቁመናን መገንባትም የየአገራቱ የቤት ሥራ መሆን እንደሚገባው ሊቀመንበሩ አሳስበዋል።

የሞሪታኒያ ፕሬዝዳንት ሞሃመድ ኦውልድ ኤል ጋዞኒ  በ2024 የአፍሪካ ሕብረትን በሊቀመንበርነት ከኮሞሮሱ ፕሬዝዳንት አዛሊ ኡሱማኒ በይፋ ተረክበዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም