የአካባቢያችንን ሰላም በመጠበቅ ለልማት እንተጋለን -- የአዳማ እና የጅማ ከተማ ወጣቶች - ኢዜአ አማርኛ
የአካባቢያችንን ሰላም በመጠበቅ ለልማት እንተጋለን -- የአዳማ እና የጅማ ከተማ ወጣቶች
አዳማ፤የካቲት 9/2016(ኢዜአ)፦የአካባቢያችንን ሰላም በመጠበቅ ልማት እንዲፋጠን የበኩላችንን ሀላፊነት እንወጣለን ሲሉ የአዳማ እና የጅማ ከተማ ወጣቶች ተናገሩ።
"እኔ ለሀገሬ ዘብ ነኝ!" በሚል መሪ ቃል ወጣቶች በሀገራዊ ሰላምና ልማት ጉዳይ የመከሩበት ውይይት በአዳማና ጅማ ከተሞች ተካሂዷል።
በአዳማ ከተማ በተካሄደ ውይይት ተሳታፊ ወጣቶች ለሀገር ሰላም ዘብ በመቆም የአካባቢያቸውን ሰላም እየጠበቁ መሆኑን ተናግረዋል።
ወጣቶቹ የአካባቢያችንን ሰላም በመጠበቅ ልማት እንዲፋጠን የበኩላችንን ሀላፊነት እንወጣለን ሲሉ ነው የተናገሩት።
በአገር ልማት ውስጥ የበለጠ ለመሳተፍ ከስራ እድል ጀምሮ አስፈላጊ ድጋፍ እንዲደረግላቸው የጠየቁት ወጣቶቹ በማህበራዊ ሚዲያ አጠቃቀም ዙሪያም ግንዛቤ የማሳደግ ስራ እንዲሰራ አንስተዋል።
የአዳማ ከተማ ወጣቶች ሊግ ኃላፊ ወጣት ኦሊፈን ግርማ የውይይቱ አላማ ወጣቱ የጋራ አንድነት በመፍጠር ሀገራዊ ሰላምን ለማስፈን አቅሙን እንዲያሳድግ መሆኑን ተናግሯል።
ከዚህም ባለፈ ወጣቱ ፅንፈኝነትና የተሳሳቱ ትርክቶችን በመታገል የጋራ አንድነትን እንዲያጠናክር ውይይቱ ማስፈለጉን አስረድተዋል።
ይህም በመሆኑ ወጣቱ የአካባቢውንና የአገሩን ሰላም በመጠበቅ የተጀመረው አገራዊ የልማት ጉዞ እንዲሳካ የበኩሉን እንደሚወጣ አስገንዝቧል።
የኢትዮጵያ ወጣቶች ሊግ ስራ አስፈፃሚ ማዕከላዊ ኮሚቴ አባል ብዙአለም ግዛቸው፣ ወጣቶች ለሰላም ቅድሚያ ሰጥተው የኢኮኖሚ ተጠቃሚነታቸውን ማረጋገጥ አለባቸው ብሏል።
ሀገሪቱ የያዘችው ሁለንተናዊ የልማት እቅድን ለማሳካት የወጣቱ ሚና ትልቅ መሆኑን በመረዳት ተሳትፎአቸውን ማሳደግ አለባቸውም ሲል ገልጿል።
በተመሳሳይ በጅማ ከተማ በተካሄደ ውይይትም ወጣቶች የአካባቢያቸውን እና የአገራቸውን ሰላም በመጠበቅ ድርሻቸውን እየተወጡ መሆኑን ገልጸዋል።
ወጣት ፈርሀን ማመኑር እንዳለው ''የአካባቢያችንንም ሆነ የሀገራችንን ሰላም ለመጠበቅ የበኩላችንን ሀላፊነት ለመወጣት ዝግጁ ነን'' ብሏል።
ወጣቶች በሰላምና በልማት ላይ ንቁ ተሳታፊ በመሆን ለአገር ብልጽግና መረጋገጥ እና ተጠቃሚነት መስራት ይገባል ነው ያለው።
ወጣቶች የመስራት፣ ሀብት የማፍራት እና የመበልጸግ ተስፋ እንዲኖረን ሰላማችንን እንጠብቃለን ያለቸው ደግሞ ወጣት አሚና አባራያ ናት።
የሰላም እና የደህንነት ጉዳይ ሁላችንንም የሚመለከት ቢሆንም ወጣቶች ደግሞ የበለጠ ሀላፊነት ያለብን መሆኑን ተረድተን ዘብ ልንቆም ይገባል ብላለች።
የጅማ ከተማ የወጣቶች ሊግ ሀላፊ ወጣት ማሀመድሳኒ ማሀመድ አሚን፣ ውይይቱ ወጣቶች የሰላም ጠባቂ መሆናቸውን ያመላከተ ነው ብለዋል።
ወጣቶች አካባቢያቸውን ተደራጅተው መጠበቅ እንዲችሉ እና ለሀገራቸው የሰላምና የዲሞክራሲ ግንባታ የበኩላቸውን ሚና እንዲወጡ የሚያስችል ውይይት መደረጉን ገልጸዋል።