በዓለም የፖለቲካና የኢኮኖሚ ኃይል አሰላለፍ ውስጥ አፍሪካ የሚገባትን ቦታ እንድታገኝ በጋራ መስራት አለብን- ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) - ኢዜአ አማርኛ
በዓለም የፖለቲካና የኢኮኖሚ ኃይል አሰላለፍ ውስጥ አፍሪካ የሚገባትን ቦታ እንድታገኝ በጋራ መስራት አለብን- ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)
አዲስ አበባ፤ የካቲት 9/2016(ኢዜአ)፡- በዓለም የፖለቲካና የኢኮኖሚ ኃይል አሰላለፍ ውስጥ አፍሪካ የሚገባትን ቦታ እንድታገኝ በጋራ መስራት አለብን ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ።
37ኛው የአፍሪካ ሕብረት የመሪዎች ጉባኤ በሕብረቱ ዋና መቀመጫ አዲስ አበባ በመካሄድ ላይ ይገኛል።
በመድረኩ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)፤ አፍሪካ በጂኦ ፖለቲካ ፣በኢኮኖሚና የአየር ፀባይ ለውጥ እንዲሁም በቴክኖሎጂ መራቀቅ ሳትበገር በተሻለ የዕድገት ጎዳና ላይ በመራመድ ላይ እንደምትገኝ ገልጸዋል።
በመሆኑም ተለዋዋጭ በሆነው የአለም የኃይል አሰላለፍ ውስጥ አፍሪካ የሚገባትን ቦታ እንድታገኝና በኢኮኖሚ አሰላለፉ ውስጥ ቁልፍ ሚናዋን እንድትወጣ ለማድረግ በጋራ መስራት አለብን ብለዋል።
አፍሪካ ሰፊ መሬት፣ እምቅ የተፈጥሮ ሃብትና በርካታ የወጣት ኃይል እያላት ተመጽዋች ልትሆን አይገባም ሲሉም ነው የተናገሩት።
አፍሪካ የሰው ልጅ መገኛ፣ ፈጠራ የተጀመረባት፣ የግብርና ስራ የተዋወቀባት፣ የመድኃኒት ቅመማ ፈር የተቀደደባት፣ መሳጭ የሆኑ የስነ ህንፃ ግንባታ ለአለም ያበረከተች ባለውለታ መሆኗንም ጠቅሰዋል።
በትምህርት፣ በሳይንስና በፈጠራ ዙሪያም ያስቀመጠችው አሻራ ለዚህ ሁነኛ ምስክሮች ናቸው ብለዋል።
የአህጉራችን የስልጣኔ ግስጋሴ በቅኝ ገዥዎች እሳቤ የተሰናከለ መሆኑን በማስታወስ የቅኝ ገዥ አገራት ይከተሉት የነበረው ስትራቴጂ የአህጉሪቱን መሰረታዊ እሳቤዎች ማጥፋት ላይ ያተኮረ እንደነበር አስታውሰዋል፡፡
የአፍሪካን ዕውቀት፣ ባህላዊና መንፈሳዊ ብቃት በማሳነስና ጥንታዊ የነበረውን የትምህርት ስነ ዘዴ በምዕራባውያን እሳቤ በመለወጥ የራሳቸውን የበላይ አድርገዋል ብለዋል።
ኢትዮጵያ ቅኝ ግዛትን በራሷ መንገድ አድዋ ላይ ባስመዘገበችው ድል መከላከል ብትችልም በተለያዩ መንገዶች የውስጥ ችግር በመፍጠር ለዘመናት ባለመረጋጋት ውስጥ እንድትቆይ መደረጓን ጠቅሰዋል።
እነዚህን ጥልቅ የሆኑ የታሪክ እውነታዎች ፈልፍሎ በማውጣት ብርሃን እንዲያዩ ማድረግ የሚያስፈልግ መሆኑን በመጥቀስ ይህም እንደ አፍሪካዊ ወደፊት ለመራመድና ክብራችንን ለማስጠበቅ መሰረት ይሆነናል ብለዋል።
አፍሪካ ምቹ የአየር ፀባይ፣ የሚታረስ መሬት፣ ውኃ፣ ደን፣ የተፈጥሮ ሃብትና ከፍተኛ ቁጥር ያለው ወጣት የሰው ሃይል ያላት በመሆኑ ይህንን ሃብት መጠቀም ከቻልን እርዳታ ፈላጊ አንሆንም ሲሉም አረጋግጠዋል።
በአለም አቀፉ የገንዘብ ስርአት ውስጥ ያለው አለመመጣጠን ገንዘብ ለማግኘት የሚደረገውን ጥረት አዳጋች አድርጎታል ሲሉም ተናግረዋል።
የአፍሪካ ህዝብ በ2050 ወደ 2 ነጥብ 5 ቢሊዮን የሚጠጋ መሆኑ በራሱ አፍሪካን በህዝብ ብዛት ቀዳሚ አህጉር ያደርጋታል ብለዋል፡፡
የአፍሪካ ማበብ ለአለም እጅጉን አስፈላጊ ነው፤ ማደግ አለብን፤ መሰረተ ልማት መገንባት አለብን ፤ የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥ አለብን፤ የጤና እና የትምህርት ስርአታችንን ማጠናከር አለብን፤ የስራ ዕድል መፍጠር አለብን፤ ነገር ግን እነዚህ ሁሉ የረጅም ጊዜ የፋይናንስ እገዛ ይፈልጋሉ ነው ያሉት።
በመሆኑም ይህንኑ ጉዳይ አለም አቀፍ የገንዘብ ተቋማት በትኩረት እንዲያዩት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ጥሪ አቅርበዋል።
አፍሪካ ዲጂታል ኢኮኖሚ ያስፈልጋታል፣ በርካታ የአፍሪካ ህዝቦች ተንቀሳቃሽ ስልክ አላቸው፣እኛም ይህን ተከትሎ ሰው ሰራሽ አስተውሎት የሚፈልገውን ከፍተኛ የዳታ ማዕከል ግንባታ ጀምረናል ብለዋል።
ከአፍሪካ አጀንዳ 2063 ጋር የተጣጣመ ከፍተኛ የሆነ የፓን አፍሪካ የዳታ ማዕከል ከገነባን በአህጉሪቱ ያለውን የዳታ ዝውውር በማፋጠንና የግለሰቦችን የዳታ ነፃነት በማስከበር ምርታማ በመሆን የአህጉሪቱን ተወዳዳሪነት ማሳደግ እንችላለን ብለዋል።
በአፍሪካ አገራት መካከል የመንገድ፣ የአየር፣ የንግድ፣ የወደብ፣ የባቡር፣ የነዳጅ ማስተላለፊያና የኮሚኒኬሽን ኔትወርክ በመገንባት የአህጉሪቷን ዜጎች ተጠቃሚ ማድረግ ይኖርብናል ሲሉ ተናግረዋል።
ከዚህ በተጨማሪ ለኢኮኖሚና ማህበራዊ ዕድገት መሰረት የሆኑትን ሰላምና መረጋጋት ማስፈን አለብን ነው ያሉት።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በንግግራቸው ኢትዮጵያ ባለፉት አምስት አመታት በትምህርት ዘርፍ ከፍተኛ ዕድገትና ለውጥ ማሳየቷን ገልጸዋል።
30 ሺህ መዋዕለ ህፃናትና አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶችን የገነባች ሲሆን በርካታ ቁጥር ያላቸው የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶችን በመገንባትና በማሻሻል ተጨባጭ ለውጥ ማሳየቷን ጠቅሰዋል፡፡
በአዳዲስ ቴክኖሎጂ የታገዘና በፈጠራ የተቃኘ ጉዞ አህጉራችንን ወደ ቀጣዩ የዕድገት ምዕራፍ ያሸጋግራታል ብለዋል፡፡
ቴክኖሎጂ የትምህርት አሰጣጡን ከፊት ለፊት ትምህርት በማውጣት ለሁሉም ተደራሽ እንዲሆን ማስቻሉን በመጥቀስ የሰው ሰራሽ አስተውሎት ራስን በራስ ለማስተማር ከመርዳቱ ባለፈ ባህላዊና የቋንቋ ተግዳሮቶችን በመሻገር ህፃናትን በትምህርት ለማነጽ እንደሚረዳ ተናግረዋል፡፡
ኢትዮጵያ ከልብ እንደምታምነው ቀጠናዊና አህጉራዊ ውህደት የኢኮኖሚ ስብጥራችንን ለማሳደግና በጎረቤት አገራት መካከል ሰላምን ለማረጋገጥ እንዲሁም የጋራ የዕድገት ግቦቻችንን ለማሳካት መሰረት ናቸው ብለዋል፡፡