ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ በታዳሽ ሀይል ልማት እና የአየር ጸባይ ለውጥን ለመከላከል የምታደርገውን ጥረት እንደሚያግዝ የአፍሪካ ልማት ባንክ አስታወቀ

አዲስ አበባ፤ የካቲት 9/2016(ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ በታዳሽ ሀይል ልማት እና የአየር ጸባይ ለውጥን ለመከላከል የምታደርገውን ጥረት እንደሚያግዝ የአፍሪካ ልማት ባንክ የሀይል፣ የአየር ጸባይና አረንጓዴ ልማት ዘርፍ ምክትል ፕሬዝዳንት ኬቨን ካሩኪ አስታወቁ፡፡

የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትር ዶክተር ኢንጂነር ሀብታሙ ኢተፋ የአፍሪካ ልማት ባንክ የሀይል፣ የአየር ጸባይና አረንጓዴ ልማት ዘርፍ ምክትል ፕሬዝዳንት ኬቨን ካሩኪ ጋር በታዳሽ ሀይል ልማት እና ተያያዥ የልማት አጀንዳዎች ላይ ውይይት አድርገዋል፡፡

ሚኒስትሩ በኢትዮጵያ የሀይል ልማት ዘርፉን በታዳሽ ሀይል ላይ ትኩረት ተደርጎ እየተሰራና የአየር ጸባይ ለውጥን ለመከላከል ብሔራዊ የአረንጓዴ አሻራ መርሃግብር አይነተኛ ሚና እየተጫወተ መሆኑን በመግለጽ የኢትዮጵያ የሃይል ልማት ፖሊሲዎችም ሆኑ አተገባበራቸው ከባንኩ ፖሊሲዎች ጋር አብረው የሚሄዱ ናቸው ብለዋል፡፡

ለዚህም የታዳሽ ሀይል ልማት እና የአረንጓዴ አሻራ መርሃግብር ጥሩ ማሳያ መሆን እንደሚችሉ ተናግረዋል፡፡

ሚኒስትሩ አክለውም የንጹህ ማብሰያ ቴክኖሎጂ ማስፋፋት ላይ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ጉዳዩን የሚከታተልና የሚተገብር አደረጃጀት ከመፍጠር ጀምሮ በትኩረት እየተሰራበት መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡

የሚኒስትሩ አማካሪ አቶ ሞቱማ መቃሳ በበኩላቸው በአፍሪካ ልማት ባንክ ጋር የሚተገበሩ የኢነርጂ ልማት ፕሮጀክቶች ጋር በተያያዘ የሚታዩ ውስንነቶችን በጋራ እያስተካከሉ መሄድ እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል፡፡

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ሀይል ዋና ስራ አስፈጻሚ ኢንጅነር አሸብር ባልቻ ተቋሙ ከልዩ ልዩ የታዳሽ ሀይል ምንጮች የሀይል ማመንጨት ስራዎች ላይ ትኩረት መደረጉን አንስተው፤ ባንኩ የጂኦተርማል ፕሮጀክቶችን እንዲደግፍ ጥያቄ አቅርበዋል፡፡

የአፍሪካ ልማት ባንክ ምክትል ፕሬዝደንት ኬቨን ካሩኪ በበኩላቸው ባንኩ ከተቋቋመበት ዋነኛ አላማ መካከል የአፍሪካ ሀገራት የኢነርጂ ልማት ላይ ድጋፍ በማድረግ ዘላቂ ልማት እንዲያረጋግጡ ለማስቻል መሆኑን ጠቅሰዋል።

ኢትዮጵያ በታዳሽ ሀይል ልማት እና የአየር ጸባይ ለውጥን ለመከላከል የምታደርገውን ጥረትም ባንኩ እንደሚያግዝ ተናግረዋል፡፡

ምክትል ፕሬዝዳንቱ አክለውም ባንኩ ከሚደግፋቸው የኢነርጂ ፕሮጀክቶች መካከል አዴል እና ደሪም ፕሮጀክቶችን አንስተው፤ ከኢትዮጵያ ጋር የሚተገበሩ ፕሮጀክቶችም ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ ገልጸዋል፡፡

ምክትል ፕሬዝዳንቱ የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ዲጂታል ኤግዚቢሽንን መጎብኘታቸውን ከሚኒስቴሩ የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም