9ኛው የኢትዮጵያ ከተሞች ፎረም በወላይታ ሶዶ ከተማ እየተካሄደ ነው - ኢዜአ አማርኛ
9ኛው የኢትዮጵያ ከተሞች ፎረም በወላይታ ሶዶ ከተማ እየተካሄደ ነው
ሶዶ፤ የካቲት 9/2016(ኢዜአ)፦ 9ኛው የኢትዮጵያ ከተሞች ፎረም በወላይታ ሶዶ ከተማ እየተካሄደ ነው።
9ኛው የኢትዮጵያ ከተሞች ፎረም ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ተመስገን ጥሩነህ እና ሌሎች የፌዴራልና የክልል ከፍተኛ የመንግስት የሥራ ሃላፊዎች በተገኙበት በወላይታ ሶዶ ከተማ እየተካሄደ ነው።
ፎረሙ "የዘመኑ ከተሞች ለኢትዮጵያ ብልጽግና" በሚል መሪ ሃሳብ በሶዶ ከተማ መካሄድ የጀመረ ሲሆን በከተሞች መካከል የፉክክርና የመደጋገፍ ባህልን በማጠናከር የከተሞችን ዕድገት የማፋጠን ዓላማ እንዳለው ተገልጿል።
ለአንድ ሳምንት በሚካሄደው ፎረም ከ120 በላይ ከተሞች በተለያዩ የልማት እንቅስቃሴዎች ተሞክሯቸውን በማቅረብ ገጽታቸውን እንደሚገነቡ ተመላክቷል።
ከተሞቹ እርስ በርስ ልምድ የሚለዋወጡበት፣ የሚደጋገፉበት፣ ወንድማማችነትና እህትማማችነት የሚያጠናክሩበት ከመሆኑ ባለፈ የኢትዮጵያን ሁለንተናዊ ብልጽግና ለማረጋገጥ ምቹ ዕድል ይፈጥራል ተብሏል።
በፎረሙ የከተሞችን ዕድገት ማሳለጥ ላይ ያተኮሩ ጥናታዊ ጽሑፎች የሚቀርቡ ሲሆን ከተሞች ለዜጎች ምቹ የመኖሪያ ስፍራ ከመሆን ባለፈ ጤናማ የፉክክር መንፈስ እንዲያጎለብቱ የሚያደርግ ነው።
ከዛሬ ጀምሮ ለአንድ ሳምንት በሚካሄደው ፎረም ከምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በተጨማሪ የከተማና መሠረተ ልማት ሚኒስትር ጫልቱ ሳኒ፣ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ እንዲሁም ሌሎች የፌዴራል፣ የክልሎች፣ የዞኖችና የወረዳዎች ከፍተኛ የመንግስት የሥራ ሃላፊዎች እየተሳተፉ ነው።
በተጨማሪም የሃይማኖት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ የሶዶ ከተማ ነዋሪዎች እና ጥሪ የተደረገላቸው ተጋባዥ እንግዶች ተገኝተዋል።