ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ አየር መንገድ በሀገር ውስጥ የ13 ቢሊዮን ብር የአየር ትራንስፖርት መሰረተ ልማት እያከናወነ ነው

አዲስ አበባ፤ የካቲት 9/2016(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዓለም አቀፍ መዳረሻዎችን ከማስፋት ባለፈ በሀገር ውስጥ የ13 ቢሊዮን ብር የአየር ትራንስፖርት መሰረተ ልማት እያከናወነ መሆኑን የአየር መንገዱ ዋና ስራ አስፈፃሚ መስፍን ጣሰው ገለጹ።

አየር መንገዱ ከመደበኛ ስራው ባሻገር 13 ቢሊዮን ብር የሚያወጣ የሀገር ውስጥ መሰረተ ልማት እየገነባ ነው። 

የኢትዮጵያ አየር መንግድ ግሩፕ ዋና ስራ አስፈጻሚ መስፍን ጣሰው፤በአፍሪካ የአቬሽን ዘርፍ ፋና ወጊ የሆነው አየር መንገዱ የኩራትም የስኬትም ምንጭ ሆኖ ቀጥሏል ብለዋል።

የኢትዮጵያ አየር መንግድ በየጊዜው የሚያጋጥሙ ፈተናዎችን በመቋቋምና በድል አድራጊነት በመሻገር እድገቱን እያፋጠነ ይገኛልም ነው ያሉት።

እኤአ በ2030 በቀረፃው ስትራቴጂክ ዕቅዱ መሰረት የመንገደኞችን ቁጥር በአራት እጥፍ፣ የአውሮፕላን ቁጥሩን በእጥፍ፣ ገቢውን ደግሞ በሶስት እጥፍ ለማሳደግ ግብ ይዞ እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

በዚህም መሰረት ዓለም አቀፍ መዳረሻዎችን በማስፋት፣ አውሮፕላኖችን በመጨመር፣ የሰው ሃይሉን በማሳደግ ላይ ይገኛልም ብለዋል።

ከባለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር አየር መንገዱ ያጓጓዛቸው መንገዶች ቁጥር 29 በመቶ፣ የውጭ ምንዛሬ ግኝቱ ደግሞ 14 በመቶ ብልጫ ማሳየቱን ዋና ስራ አስፈፃሚው ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ በዓለም ከ130 በላይ መዳረሻዎች እንዲሁም በሀገር ውስጥ 22 የበረራ መዳረሻ ያለው መሆኑን ጠቅሰዋል።

በሀገር ውስጥ መሰረተ ልማት ግንባታም በቦሌ ኤርፖርት ብቻ 350 ሚሊዮን ዶላር የማስፋፊያ ስራዎችን ማከናወኑን ገልጸዋል።

የተርሚናሎችና መንደርደሪያዎችን ግንባታ ጨምሮ የ13 ቢሊዮን ብር የአየር ትራንስፖርት መሰረተ ልማት እያከናወነ መሆኑን አቶ መስፍን ተናግረዋል።

በሀገር ውስጥ የተሻለ የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴ ባለባቸው ከተሞች የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንትን በማሳለጥና ምርቶች ለገበያ እንዲቀርቡ በማስቻል አየር መንገዱ ከፍተኛ ሚናውን እየተወጣ ይገኛልም ነው ያሉት።

 

 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም