ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ በታዳሽ ኃይል ልማት ውጤታማ ስራ እያከናወነች ነው - ኮሚሽነር አቡ ዘኢድ አማኒ(ዶ/ር)

አዲስ አበባ፤ የካቲት 8/2016(ኢዜአ)፡- ኢትዮጵያ በታዳሽ ኃይል ልማት ውጤታማ ስራ እያከናወነች መሆኑን በአፍሪካ ሕብረት የመሰረተ ልማትና ኢነርጂ ኮሚሽነር አቡ ዘኢድ አማኒ (ዶ/ር) ተናገሩ።

በመግለጫቸውም ኃይል፣ መሰረተ ልማት፣ ትራንስፖርት እንዲሁም ዲጂታላይዜሽን ፈጣን እና አካታች ልማት ለማምጣት ያላቸውን ሚና ገልጸዋል።

ተጽዕኖን የሚቋቋምና ቀጣይነት ያለው አካታች መሰረተ ልማት ለአፍሪካ ሁለንተናዊ ብልጽግና፣ የስራ ዕድል ፈጠራ እንዲሁም የአየር ንብረት ለውጥ ተጽእኖን ለመቋቋም የጀርባ አጥንት መሆኑን አንስተዋል።

በአፍሪካ ያለውን የኃይል ተደራሽነት ለማስፋት የታዳሽ ኃይል ልማትን ጨምሮ ለሌሎች ዘርፎች ትኩረት እንደተሰጣቸው ተናግረዋል። 

በተፈጥሮ ጋዝ፣ በኒውክሌር ኢነርጂና ሌሎች ዘርፎች ያለውን እምቅ ሃብት ለመጠቀም የተጀመሩ ስራዎች መኖራቸውን ገልጸዋል።

 በታዳሽ ኃይል ልማት መልካም ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑን በመግለጽ በተለይም ኢትዮጵያን ጨምሮ በ12 አፍሪካ ሀገራት እየተከናወኑ ያሉ ተግባራት የሚያበረታቱ መሆናቸውን ጠቁመዋል።

 ኮሚሽኑ በ2023 ተጽእኖን የሚቋቋምና ቀጣይነት ያለው መሰረተ ልማትን በአፍሪካ ከማስተዋወቅ አንጻር ተስፋ ሰጪ ስራ መስራቱን ተናግረዋል።

በአፍሪካ በመሰረተ ልማትና በሃይል ዘርፍ ያለውን የኢንቨስትመንት አማራጭ በመጥቀስ በመንግስትና በግል አጋርነት ያለው ትብብር እንዲጠናከር ጥሪ አቅርበዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም