በደቡብ ወሎ ዞን ለተጠለሉ ተፈናቃዮች የምግብ እህል ድጋፍ ተደረገ - ኢዜአ አማርኛ
በደቡብ ወሎ ዞን ለተጠለሉ ተፈናቃዮች የምግብ እህል ድጋፍ ተደረገ
ደሴ ፤ የካቲት 8/2016(ኢዜአ)፡- የኢትዮጵያ ልማት ባንክ በደቡብ ወሎ ዞን ለተጠለሉ ተፈናቃይ ወገኖች ከአራት ሚሊዮን ብር በላይ ወጭ የተደረገበት የምግብ እህል ድጋፍ አደረገ።
ድጋፉን ያስረከቡት በኢትዮጵያ ልማት ባንክ የደሴ ዲስትሪክት ተወካይ ሥራ አስኪያጅ አቶ የኋላሸት ወርቁ እንደገለጹት፤ ባንኩ ለተፈናቃዮች ድጋፍ እያደረገ ነው፡፡
በዚህም ከተለያየ አካባቢ ተፈናቅለው በዞኑ ተሁለደሬ ወረዳ ጃራ ቁጥር አንድ እና ሁለት፣ ኩታበርና ሀርቡ ከተማ ጊዜያዊ መጠለያ ካምፕ ለተጠለሉ 3 ሺህ 139 ተፈናቃዮች የሚውል የምግብ እህል ዛሬ ድጋፍ መደረጉን ገልጸዋል፡፡
ድጋፉም ለአንድ ወር የሚበቃ 470 ኩንታል ዱቄትና 47 ኩንታል ምስር፣ 1 ሺህ 569 ሊትር የምግብ ዘይት መሆኑን ጠቁመው፤ ለዚህም ከአራት ሚሊዮን ብር በላይ ወጭ መደረጉን ተናግረዋል፡፡
ድጋፉን የተረከቡት የደቡብ ወሎ ዞን አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ተጠሪ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ አሊ ሰይድ በበኩላቸው፤ መንግስት ባለድርሻ አካላትን ጭምር በማስተባበር ለተፈናቃይ ወገኖች ድጋፍ እንዲደርስ እየተደረገ ነው።
በዚህም ኢትዮጵያ ልማት ባንክ ዛሬ ድጋፍ ማድረጉን ጠቁመው፤ ሌሎችም ሰብዓዊ ድጋፍ በማድረግ ማህበራዊ ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ አሳስበዋል።
ሀርቡ ከተማ ተጠልለው የሚገኙት አቶ አህመድ ዳውድ በሰጡት አስተያየት፤ ዛሬ የተደረገላቸው ድጋፍ ችግራቸውን ለማቃለል ያግዛቸዋል፡፡
ለተደረገላቸው ድጋፍ አመስግነው፤ ድጋፉ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል።
ሌላዋ የድጋፋ ተጠቃሚ ወይዘሮ አሚናት በሽር በበኩላቸው፤ የተደረገላቸው ድጋፍ አሁን ያለባቸውን የምግብ አቅርቦት ክፍተት እንደሚሞላ ተናግረው፤ ለተደረገላቸው ድጋፍ አመስግነዋል፡፡